የዩናይት ስቴትስ ብሄራዊ የደህንነት አማካሪ ጄክ ሰለቨን ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዪ ጋር ለመነጋገር በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቻይና እንደሚጓዙ ስለ ጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ተናገሩ፡፡
ንግግሩ በዚህ ዓመት መጨረሻ በፕሬዝዳንት ባይደን እና በቻይናው አቻቸው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ መካከል ሊደረግ የሚችለውንም ስብሰባ ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የታቀዱት ስብሰባዎች የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነቶችን ለማረጋጋት በተከታታይ ከታቀዱት የከፍተኛ ደረጃ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች የቅርብ ጊዜዎቹ ናቸው፡፡
“ሰፊ እና ስልታዊ ነው” ተብሎ የተገለፀው ንግግር ቻይና በኒውክሌር ደህንነት እና አጠቃላይ ደህንነት ላይ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ውይይት ካቆመች በኋላ የመጣ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ቻይና ባላፈው ሀምሌ ከዋሽንግተን ጋር የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ድርድር ለጊዜው ማቆሟን አስታውቃለች፡፡
የቀድሞ የሲአይኤ የቻይና ተንታኝና አሁን የጆርጅ ታወን ዩኒቨርስቲ መምህር ደኒስ ዊልደር "ዩናይትድ ስቴትስ በስትራቴጂካዊ መረጋጋት ላይ የተጠናከሩ ውይይቶችን ማድረግ ብትፈልግም ቻይናውያኑ ያመነታሉ፡፡ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀም አይቻልም ስለሚለው ስምምነት አስቀድመው መወያየትን ይመርጣሉ፣ ያንን መርህ ግን ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም” ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡
“በዚህም ምክንያት ጥቂት ቡድኖች ባደረጓቸው ስብስባዎች የተገኙ መሻሻሎች ላይ ትንሽ እንቅፋት ተፈጥሯል፡፡” ሲሉ ዊልደር አክለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም