ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልታናት በዚህ ሳምንት ወደ ቻይና እንደሚያቀኑ መንግስት አስታውቋል። በሁለቱ ሃገራት መካከል ውጥረቱ እንዳለ ቢሆንም፣ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚዎች በሆኑት ሁለቱ ወገኖች መካከል ግንኙነታቸውን ጠብቆ ለማቆየት ያለመ ነው ተብሏል።
ወደ ሻንጋይ የሚደረገው ጉዙ በሁለቱ ሃገራት መካከል ባለፈው ዓመት የተመሠረተውና በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ በሚሠራው ቡድን አማካይነት በንግድ እንዲሁም መነሻው ከቻይና እንደሆነ በሚነገርለትና አሜሪካ ውስጥ ትልቅ የጤና ቀውስ በመፍጠር ላይ ባለው ፈንትነል የተሰኘውን ሱስ አስያዥ መድሃኒት በተመለከተ ይነጋገራሉ ተብሏል።
በመጪው ሐሙስ እና ዓርብ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የአሜሪካ ግምጃ ቤት፣ የፌዴራል የፋይናንስ ቁጥጥር መሥሪያ ቤትና የሌሎችም ተቋማት ባለሥልጣናት እንደሚገኙ ታውቋል።
የንግድ እና የፋይናንስ ችግሮች በሚስተዋሉበት ወቅት በሁለቱ ሃገራት መካከል የተሻለ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር በሚያስችሉና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩም ተመልክቷል።
ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የጋራ ቡድን ሲገናኝ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑንና፣ በቻይና ሲካሄድ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም