አሜሪካ ታዋቂውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ ዛሬ አስባ ውላለች፡፡ ቀኑ በሰልፍ፣ በጸሎት እና በሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ሲከበር ይውላል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፊላደልፊያ በሚገኝ በአንድ ችግረኞችን በሚመግብ ድርጅት፣ በበጎ ፈቃደኝነት ሥራ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ በደቡብ ካሮላይና በመገኘት ዜጎች ድምፃቸውን ለፍትህ እና በመሠረታዊ መብቶች ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን ለመታገል እንዲጠቀሙ የሚያበረታታ ንግግር እንደሚያደርጉ ከዋይት ሃውስ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
“አሜሪኮርፕ” በተሰኘው የበጎ አድራጊ ድርጅት አማካይነት ዜጎች በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ይሳተፋሉ።
በየዓመቱ በጥር ወር ሦስተኛው ሰኞ፣ አሜሪካውያን በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ሰላማዊ ትግል በመምራት፣ የዘር ልዩነትን በመታገል እና ለጥቁሮች መብት መከበር እንዲሁም በምርጫ የመሳተፍ መብትን ለማስከበር ትግል ያደረገውን ማርቲን ሉተር ኪንግ ያስባሉ።
መድረክ / ፎረም