በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን ከማሪዮፑል ተጨማሪ ሰዎች ይወጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቀች


የዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ ናንሲ ፐሎሲ፤ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ
የዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ ናንሲ ፐሎሲ፤ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ

የዩክሬን ባለሥልጣናት ከተከበበቸው ማሪዮፑል ከተማ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መውጣት ይችላሉ ብለው እንደሚጠበቁ ተናገሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ባላፈው እሁድ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መውጣት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የሩሲያ ወታደሮች ቀሪውን የማሪዮፑል ከተማ የተቆጣጠሩ ቢሆንም፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችና፣ 2ሺ የሚደርሱ የዩክሬን ወታደሮች አሁንም በአዞቭስታል የብረታ ብረት ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ሰላማዊ ሰዎቹን በቅርቡ ለማስወጣት የተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች ቢኖሩም፣ ብዙም አለማምጣታቸውን ገልጸው ገልጸው ሩሲያን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

ዘለነስኪ በእሁዱ መግለጫቸው “በዚህ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ቀናት የተካሄደ እውነተኛ የተኩስ አቁም ነበር” ብለዋል፡፡ የዩክሬን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አርያና ቨርሽክ በአቮስታ ያለው ሁኔታ “ምግብ፣ ውሃና መድሃኒት ለተሟጠጠባቸው ሰዎች የገጠማቸው እውነተኛው ሰብአዊ ቀውስ ነው” ብለዋል።

የተባበሩ መንግሥታት ድርጅትና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ሰላማዊ ሰዎች እንዲወጡ የተደረገበት የእሁዱን እምርጃ “ደህንነቱ የተጠበቀና ሰለማዊ” ብሎታል፡፡

ለሁለት ወራት በከተማው ላይ የዘነበው የቦምብ ጥቃት ቢኖርም፣ በማሪዮፑል ሰሜናዊ አቅጣጫ፣ በአዞቭ ባህር ዳርቻ፣ አሁን ድረስ 100ሺ የሚደርሱ ሰላማዊ ዩክሬናውያን እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ ናንሲ ፐሎሲ፣ ከስድስት የዴሞክራቲክ ህግ አውጭ አባላት ጋር በመሆን፣ ባላፈው ቅዳሜ በኪየቭ ድንገተኛ ጉብኘት በማድረግ፣ ከፕሬዚዳት ዘለንስኪ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡

ዛሬ ሰኞም ከፖላንድ ፕሬዚዳንት አንድርዜዥ ዱዳ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፣ የሩሲያን ወረራ በመመከት ላይ ለምትገኘው ዩክሬን፣ የኔቶ ተባባሪ አገሮች ለሚያደርጉት እገዛ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

ፐሎሲ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ “ሩሲያ እሳካሁን የሠራቸው ሥራ በፍጹም ሊታገሱት የማይገባ መሆኑን፣ ጠንካራ ወታደራዊ ምላሽ እንደሚያስፈልግ፣ ጠንካራ ማዕቀብ መጣል እንደሚያስፈልግ አስመስክራለች” ብለዋል፡፡

“ከሩሲያ የሚመጣውን ሥጋት አስመልክቶ፣ ከዚህ ያነሰ ነገር ልናደርግ አንችልም” ያሉት ፐሎሲ “አስጊነታቸውን ከወዲሁ በተግባር አሳይተዋል፣ ህጻናትን፣ ቤተሰቦችን፣ ሰላማዊ ሰዎችንና ሌሎችን ገድለዋል፡፡ ስለዚህ ትናንት እንደተናገርኩት በጥቃት ለሚያስፈራራ ባዶ ምላሽ አንሰጥም” ብለዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰዎች ተሰደዋል፡፡ ከዚያ ውስጥ ሶስት ሚሊዮን የሚቆጠሩት የሄዱት ወደ ፖላንድ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል፡፡

ከፖላንድ ቀጥሎ 800ሺ የሚደርሰውን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኛ የተቀበለችው ሩማኒያ ናት፡፡

ዋይት ኃውስ ዛሬ ሰኞ እንዳስታወቀው ቀደማዊት ዕመቤት ጂል ባይደን በመጭው ሀሙስ ወደ ሮማንያና ስሎቮኪያ ያመራሉ፡፡

ባይደን በሩሲያው ወረራ ሳቢያ ከዩክሬን ከተፈናቀሉ ስደተኞች ጋር እንዲሁም ስደተኞችን ከሚረዱ የአገሬው ተወላጆች፣ ቤተሰቦች፣ የእርዳታ ሰራተኞችና ዩክሬናውያን ህጻናት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከሚያደርጉ መምህራን ጋር እንደሚነጋገሩ ተገልጿል፡፡

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረርችበት ካለፈው የካቲት ጀምሮ ዩክሬንን በመጎብኘት ፐሎሲ ትልቋ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ፐሎሲ ዩክሬንን በለቀቁበት ወቅት ለዘለንስኪ “በዚህ ጦርነት በአሸናፊነት እስክንወጣ ድረስ ከጎንዎ ነን” ብለው መናገራቸው ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG