በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የብሪታኒያው ጆንሰን "የሩሲያን ጠብ አጫሪነት ለመመከት" የታለመ የአንድነት ጥሪ አሰሙ


የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን

ሩሲያ የዩክሬንን ሉዓላዊነት በመጋፋት በምታደርገው እንቅስቃሴ “ግጭት እና ደም መፋሰስ ከሚያስከተል መንገድ” ይልቅ የዲፕሎማሲን አማራጭ እንድትወስድ ብሪታንያ አሳሰበች።

"በመሰረቱ በዩክሬን የሚካሄድ ጦርነት ለሩሲያ እና ለዩክሬን ህዝብ ብሎም ለአውሮፓ ደኅንነት አደገኛ ነው። እናም በዩክሬን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ወረራ ከፍተኛ መዘዝ እንደሚያስከትል እና ብርቱ ዋጋ እንደሚያስከፍል ኔቶ በአንድ ድምጽ ግልጽ አድርጓል" ሲሉ የብሪታኒያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በተገናኙበት ወቅት ተናግረዋል።

ምዕራባውያን መንግሥታት ሩሲያ ከዩክሬይን ድንበር አቅቢያ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ወታደሮችን በማከማችት እና የጦር መርከቦቿን ወደ ጥቁር ባህር በማሰማራት፤ እንዲሁም በዛሬው ዕለት ለጀመረችው ወታደራዊ ልምምድ ተጨማሪ ጦር እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ወደ ቤላሩስ በመላክ የፈጠረችውን ቀውስ ለማርገብ እርምጃ ትወስድ ዘንድ እየጠየቁ ነው።

ዩክሬንም በበኩሏ የራሷን ወታደራዊ ልምምድ ዛሬ ጀምለች። በሁለቱም ወገን የሚካሄዱት የጦር ልምምዶች እኤአ እስከ የካቲት 10/2014 እንደሚዘልቁ ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ በዛሬው ዕለት በሰጡት አስተያየት፣ "እርስ በእርስ በመከባበር የሚደረግ ንግግር" ብቻ ነው “ጤናማ” ወዳሉት ግንኙነት “ሊያመራ የሚችለው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ርዕዮተ-ዓለማዊ ይዘት ያላቸው አቀራረቦች፣ ማስጠቀቂያ እና ማስፈራሪያዎች የትም የማያደርሱ መንገዶች ናቸውም ብለዋል።

ዛሬ ሃሙስ ከፖላንድ እና ከኔቶ መሪዎች ጋር ተገናኝተው የሚነጋገሩት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ጽ/ቤታቸው "የሩሲያ ጥቃት የደቀነውን ፈተና ለመቋቋም ከኔቶ አጋሮች ጋር በአንድ መቆም" ያለውን ጥሪ አሰምተዋል።

ጆንሰን በጎረቤት ዩክሬን ላይ ሩሲያ በምታደርገው ወረራ ሳቢያ ሊከሰት ለሚችል የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆኑ አንድ ሺህ የብሪታንያ ወታደሮች ዝግጁ እንዲሆኑ አዘዋል።

“ማየት ያለብን እውነተኛ ዲፕሎማሲን እንጂ አንዳች ጥቅም ለማግኘት በሚል የሚውጠነጠን የማስገደድ ወይም እጅ የመጠምዘዝ ዲፕሎማሲን አይደለም” ያሉት ጆንሰን በመግለጫቸው አክለውም "እንደ ጥምረት መታለፍ የሌለበትን ሥፍራ የሚያሳየውን መስመር ከበረዶው ላይ አስምረን፣ የማንደራደርባቸው መርሆዎች መኖራቸውን ግልጽ ማድረግ አለብን። ይህም የእያንዳንዱን የኔቶ አጋር ደህንነት እና ኔቶን በአባልነት ለመቀላቀል የሚሻ የእያንዳንዱን አውሮፓዊ ሃገር መብት ይጨምራል" ብለዋል።

በሌላ ተያያዥ ዜና፡ የዋይት ሃውሷ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ትናንት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ ሩሲያ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነች። ያም ሁኔታ ይለወጣል ብላ ዩናይትድ ስቴትስ ተስፋ ታደርጋለች ብለዋል።

“ለወታደራዊ ልምምዶች የሚደረገውን ዝግጅት እንከታተላለን። ይህም በእርግጠኝነት ግጭት ወደ መቀስቀስ የሚያመራ እንጂ ግጭት ለማርገብ የሚያግዝ እርምጃ አይደለም”ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ።

በሌላ በኩል የሩሲያ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ቁጥሩ ሰላሳ ሺህ የሚደርሰው ጦራቸው ከቤላሩስ ጦር ኃይል ጋር በጋራ የሚያደርጉትን ወታደራዊ ልምምድ ለማስፈጸም ትላንት ቤላሩስ መግባታቸው ተዘግቧል።

ሩሲያ ለወታደራዊ ልምምዱ S-400 የተባሉ ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፉ የሚሳኤል ጦር መሳሪያዎችን እና በርካታ ተዋጊ ጄቶችን ወደ ቤላሩስ ልካለች። የሩሲያ ጦር ኃይሎች ዋና አዛዝ ጀነራል ቫለሪ ጌራሲሞቭ ወታደራዊ ልምምዱን እንደሚመሩም ታውቋል።

ከዋና ከተማይቱ ኪየቭ በስተደቡብ 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሥፍራ ጎረቤት ቤላሩስ ውስጥ የሚደረገው ይህ የጦር ልምምድ ዩክሬይን ላይ የተደቀነውን የጦርነት አደጋ ቅርብ ከሚያደርጉ እርምጃዎች አንዱ ተደርጎ ታይቷል።

በምላሹም የዩክሬን ጦር ዛሬ የጀመረው የጦር ልምምድ የኪየቭ አጋር በሆኑ ምዕራባውያን የሚቀርቡ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ፀረ ታንክ ሚሳኤሎች የሚሳተፉበት መሆኑ ታውቋል።

XS
SM
MD
LG