በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ የዩክሬንን ወደቦች ልትከፍት እንደምትችል ቦሬል ተስፋ አላቸው


ፎቶ ፋይል፦ የእህል ባቡር ፋይል በኦዴሳ ክልል፣ እአአ ሰኔ 22/2022
ፎቶ ፋይል፦ የእህል ባቡር ፋይል በኦዴሳ ክልል፣ እአአ ሰኔ 22/2022

ሩሲያ ኦዴሳንና ሌሎችም የዩክሬን ወደቦችን ለመክፈት በዚህ ሣምንት ትስማማለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ዛሬ ሰኞ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

እርምጃው ብዙ አገሮች ውስጥ ለተፈጠረው የምግብ እጥረት መፍትኄ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ቦሬል ብራስልስ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ሩሲያ የዩክሬን እህል እንዲወጣ መፍቀድ አለባት ወይም ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ‘ሩሲያ ስለ ሰው ልጆች ምንም ደንታ ሳይሰጣት ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው’ ብሎ መናገር ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

ይህ “የዲፕሎማሲ ጨዋታ አይደለም። ለብዙ ሰዎች የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው” ብለዋል ቦሬል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ከቱርክና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር የሩሲያ ወረራ ከተጀመረበት ከየካቲት 17/2014 ዓ.ም. አንስቶ በዩክሬን ጎተራዎች ውስጥ የተከማቸውን በሚሊዮኖች ቶኖቾ የሚገመት እህል ኤክስፖርት ለማድረግ “አጠቃላይ ስምምነት” መኖሩን ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አሁን በሩሲያ ላይ የተጣሉትን ማዕቀቦች አፈፃፀም ለማጠናከርና እንዲሁም በሩሲያ ወርቅ ሽያጭ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንዲጣል ከማቀድ ጋር ለዩክሬን ወታደራዊና ተጨማሪ እገዛ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ብራስልስ ተቀምጠዋል።

“ሩሲያ አውሮፓዊያን በሩሲያ ጋዝ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት በመጠቀም በአውሮፓ ኅብረት አገሮች አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እየተጠቀመችበት ነው” ያሉት ቦሬል ይሁን እንጂ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች “ሊገጥም የሚችለውን ማናቸውንም ችግር ለመቋቋም” ዕቅድ በማውጣት እየተዘጋጁ መሆናቸውንና ዩክሬንን መደገፋቸውን እንደማያቆሙ ገልፀዋል።

ቦሬል አክለውም የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የሚያደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም “ትዕግሥትና ፅናት ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።

የአውሮፓ ሚኒስትሮች ዩክሬን ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መረጃዎችን ከዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሮ ኩሌባ እያገኙ መሆናቸውን ቦሬል አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን የዩክሬን ቀዳማዊት እመቤት ኦሌና ዜለንስካን ዛሬ ሰኞ ዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀብለው እንደሚያነጋገሩ ተገልጿል።

ዩክሬን ውስጥ ሩሲያ ስሎቭያንስክና ኻርኪቭን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎችን በከባድ መሣሪያ እየደበደበች መሆኑን የዩክሬን ጦር ዛሬ ሰኞ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG