በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስና ግብጽ በሱዳን የጋራ ፍላጎት አላቸው


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ "ዩናይትድስ ስቴትስና ግብጽ በሱዳን ወታደራዊ ግልበጣ የተደናቀፈው የሱዳን የዴሞክራሲ ሽግግር፣ ወደ ቦታው እንዲመለስ የጋራ ፍላጎት አላቸው" ሲሉ ተናገሩ፡፡

ብሊንከን ይህን ይህን የተናገሩት፣ እሳቸውና የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ በተገኙበት፣ ትናንት ሰኞ በዋሽንግተን በተከፈተው የዩናይትድ ስቴትና የግብጽ የስትራቴጂክ ምክክር መድረክ ላይ ነው።

ትናንት ሰኞ በዩናይትድ ስቴትስና ግብጽ መካከል የተካሄደው የጋራ ስትራቴጂክ ምክክር እኤአ ከ2015 ወዲህ የመጀመሪያው ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን “እኤአ ጥቅምት 25 በሱዳን የተደረገው ወታደራዊ ግልበጣ በአደገኛ ሁኔታ አለመረጋጋት እየፈጠረ ነው” ሲሉ የተናገሩት በዚህ መድረክ ላይ ነው፡፡

ብሊንከን “ጀግንነትና ጥንካሬ በታየበት ሁኔታ፣ በተደጋጋሚ ወደ አደባባይ በመውጣት፣ ተቃውሞውን የገለጸውን የሱዳን ህዝብ ፍላጎት ማሟላት የሚቻልበት፣ ብቸኛው መንገድ፣ ሲቪል መሩን የሽግግር መንግሥት ወደ ቦታው መመለስ ሲቻል ብቻ ነው” ብለዋል፡፡

በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ፣ ሳኡዲ አረብያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬት “በሱዳን በሲቪል የሚመራው የሽግግር መንግሥት ተቋማት በአስቸኳይ ወደቦታቸው ይመለሱ” በሚል የጋራ መግለጫ ሲያወጡ፣ በጋራ መግለጫው ላይ ካልተሳተፉ የአካባቢው አገሮች መካከል ግብጽ አንዷ ናት፡፡

በዎል ስትሪት ጆርናል የወጣው አንድ ዘገባ የሱዳን ወታደራዊ አዛዥ ጀኔራል አብደል ፈታ አልቡርሃን፣ የመንፈንቅለ መንግሥቱን ከማካሄዳቸው አንድ ቀን በፊት፣ የግብጹን ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ይሁንታና ድጋፍ ማግኘታቸውን አመልክቷል፡፡

በትናንቱ መድረክም የተገኙት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ፣ ስለሱዳን ወታደራዊ ግልበጣ የተናገሩት አንድም ቃል የሌለ ሲሆን፣ ለጋዜጠኞች ጥያቄም የሰጡት ምላሽ የለም፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ “በሱዳን የሲቪል አስተዳደሩን ወደቦታው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት አስመልክቶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከግብጽ ባለሥልጣናት ጋር ትወያያለች” ብለዋል፡፡

የዩናትድ ስቴትስ በሱዳን በተካሄደው ወታደራዊ ግልበጣ ሳቢያ፣ የ700ሚሊዮን ዶላር የምጣኔ ሀብት እርዳታን ወዲያውኑ እንዲቋረጥ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

በሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የሚደረገው ምክክር፣ የሰብአዊ መብትና በምጣኔ ሀብት በደህንነትና ባህላዊ ጉዳዮች የጋራ ትብብርን ለማጎልበት በሚቻልበት ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ያተኮረ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ብሊንከን ግብጽ ለአካባቢው መረጋጋት የምትጫወተውን ሚና አድንቀው በጋዛ ተከስቶ የነበረውን ውጥረት በማርገብ ያደረገቸውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG