በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሜሪላንድ ቦልቲሞር አቅራቢያ አንድ ትልቅ ድልድይ ተደርምሶ ጉዳት አደረሰ


ፍራንሲስ ስኮት ኪ ብሪጅ በዩናይትድ ስቴትስ ምስራቃዊ ክፍለ ግዛት ሜሪላንድ የባልቲሞር ከተማ የሚገኘው ድልድይ እአአ መጋቢት 3/2024
ፍራንሲስ ስኮት ኪ ብሪጅ በዩናይትድ ስቴትስ ምስራቃዊ ክፍለ ግዛት ሜሪላንድ የባልቲሞር ከተማ የሚገኘው ድልድይ እአአ መጋቢት 3/2024

በዩናይትድ ስቴትስ ምስራቃዊ ክፍለ ግዛት ሜሪላንድ ውስጥ በሚገኘው የባልቲሞር ከተማ አቅራቢያ ዛሬ ማክሰኞ ፍራንሲስ ስኮት ኪ ብሪጅ የተባለው አንድ ትልቅ ድልድይ ተደርምሶ ወድቋል፡፡

በድልድዩ ላይ ወድቆ በነበረበት ወቅት በርካታ ተሽከርካሪዎች በድልድዩ ላይ እንደነበሩ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች ሁኔታቸው ያልታወቀ ሰባት ሰዎችን ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ባለሥልጣናት ገለጸዋል።

አደጋው የደረሰው ፓታፕስኮ በተባለው ወንዝ ውስጥ የነበረውና ዳሊ የተባለው የሲንጋፖርን ባንዲራ የሚያውለበልብ እቃ አጓጓዥ መርከብ ከድልድዩ ደጋፊ አምድ ጋር በመጋጨቱ ነው፡፡

የባልቲሞር ከተማ የእሳት አደጋ መከላከያ ኃላፊ ጄምስ ዋላስ አደጋው ከደረሰ ሰዓታት በኋላ ሁለት ሰዎች ከውሃ ውስጥ እንዲወጡ መደረጉን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ከሁለቱ ሰዎች መካከል አንደኛው ከባድ ጉዳት ያገኛቸው በመሆኑ ወደ ህክምና ማዕከል ሲወሰዱ ሌላኛው ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም፡፡

የነፍስ አድን ጠላቂዎች ከ9 ዲግሪ በታች ከሆነው ከወንዙ ውሃ ቅዝቃዜ ጋር በመጋፈጥ ሁኔታቸው ያልታወቁ ሌሎች ሰዎችን እያፈላለጉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሜሪላንድ አገረ ገዥ ዌስ ሙር የአስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል፡፡

ክፍለ ግዛቱ ከባይደን አስተዳደርና ከሌሎች የአስቸኳይ ነፍስ አድን ቡድኖች ጋር በመሆን የፌደራል ኃይሎችን በፍጥነት አሰማርቶ እየሰራ መሆኑንም አገረ ገዥው ተናግረዋል፡፡

የባልቲሞር ከንቲባ ብራንደን ስኮት ክስተቱን "የማይታሰብ አሳዛኝ" ብለውታል።

የባልቲሞር ፖሊስ ኮሚሽነር ሪቻርድ ዎርሊ ከድልድዩ ምሶሶ ጋር የተፈጠረው የመርከቡ ግጭት ሆን ተብሎ የተደረገ ስለመሆኑ "ምንም ምልክት የለም" ብለዋል።

ከድልድዩ አንደኛው ምሶሶ ጋር የተጋጨውን መርከብ ይመሩ የነበሩት ሁለቱ የመርከቡ ካፕቴኖችን ጨምሮ ሁሉም የመርከቢቱ ሠራተኞች ምንም አደጋ ያላገኛቸውና በደህና ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የዳሊ መርከብ ባለቤት የሆነው የሲነርጂ ማሪን ኮርፕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

47 ዓመቱን ያስቆጠረውና 2.5 ኬሎሜትሮች ርዝመት ያለው ድልድይ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ትላልቅ የወደብ ከተሞች አንዷ የሆነችው ባልቲሞር ከተማን በመዞር ወደ ተለያዩ ክፍለግዛቶች የሚወስዱ ትላልቅ አውራጎዳናዎችን የሚያገናኝ ነው፡፡

“ኪ ብሪጅ” እየተባለ ባጭሩ የሚጠራው ድልድይ የተሰየመው የዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ መዝሙር “The Star Spangled Banner,” የተባለውን ግጥም በጻፈው ፍራንሲ ስኮት ኪ (Francis Scott Key) ስም ነው፡፡

ስኮት ግጥሙን የጻፈው እኤአ ከ1812 ጀምሮ በሀገራት መካከል የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ የእንግሊዝ ጦር እኤአ በ1814 ባልቲሞር በነበረው ትልቅ የአሜሪካ ምሽግ ላይ የሰነዘረውን ከባድ የቦምብ ጥቃት ከተመለከተ በኋላ ነው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG