በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽንስ ማቋረጥን ህገ መንግሥታዊ መብት ያደረገውን ታሪካዊ ውሳኔ ሻረው


የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሀገሪቱ ሴቶች የፅንስ የማቋረጥ ህገ መንግሥታዊ መብት የሰጠውን እአአ የ1973ቱን ሮ ቪ ዌድ ተብሎ የሚጠራውን ውሳኔ በዛሬው ዕለት ሽሮታል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሀገሪቱ ሴቶች የፅንስ የማቋረጥ ህገ መንግሥታዊ መብት የሰጠውን እአአ የ1973ቱን ሮ ቪ ዌድ ተብሎ የሚጠራውን ውሳኔ በዛሬው ዕለት ሽሮታል።

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሀገሪቱ ሴቶች የፅንስ የማቋረጥ ህገ መንግሥታዊ መብት የሰጠውን እአአ የ1973ቱን ሮ ቪ ዌድ ተብሎ የሚጠራውን ውሳኔ በዛሬው ዕለት ሽሮታል። በዚህ በዛሬው ውሳኔውም ፍርድ ቤቱ ላለፉት ሃምሳ ዐመታት በህግ የተፈቀደ ሆኖ የኖረውን ጽንስን ማቋረጥን የመፍቀድ ወይም የመከልከል ስልጣን የየክፍላተ ሀገሩ (የስቴቶቹ) ፋንታ አድርጎታል።

ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወግ አጥባቂ ዳኞች አንዱ የሆኑት ዳኛ ሳሙኤል አሊቶ ባቀረቡት እና ሌሎች አራት ወግ አጥባቂ ዳኞች በደገፉት የውሳኔ አስተያየታቸው "ህገ መንግሥቱ ስለ ፅንስ ማስወረድ የሚናገረው ነገር የለም። እንዲህ ያለውን መብት በተዘዋዋሪ የሚያስጠብቅ አንዳችም የህገ መንግሥት አንቀጽም የለም።" ብለዋል።

የዚህ የዳኛ አሊቶ የውሳኔ አስተያየት ረቂቅ ከሁለት ወራት ገደማ በፊት በድብቅ አንድ የዜና አውታር እጅ መድረሱን ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ የጽንስ ማቋረጥ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ሲያሰሙበት ቆይተዋል።

በዕርግጥ እአአ በ1973 ጀመሮ ፀንቶ የቆየውን ሮ ቪ ዌድ ተብሎ የሚጠራውን የራሱን ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መቀልበሱ ፅንስ ማቋረጥን አያግድም። ይሁን እንጂ በመላ ሀገሪቱ ጉዳዩን በሚመለከቱ ህግጋት ላይ አንድምታው ሳይውል ሳያድር መምጣቱ የማይቀር ነው።

ገትማከር ኢንስቲቲዩት የተባለው የሴቶች የጽንስ ማቋረጥ መብት ደጋፊ የምርምር ተቋም እንደሚለው አብዛኞቹ በደቡብ እና በማእከላዊ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሀያ ስድስት ክፍላተ ሀገር (ስቴቶች) ሮ ቪ ዌድን ከሚሰርዘው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ጽንስ ማስወረድን በህግ እንደሚከለክሉ አመልክቷል። ያ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶች ጽንስ የማቋረጥ መብታቸው ወደሚከበርበት የሀገሪቱ አካባቢ ለመጉዋዝ ይገደዳሉ።

ለዘብተኞቹ ወይም ሊብራሎቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ዳኛ ስቴፈን ብራየር፥ ሶኒያ ሶቶማዮር እና ኤሌና ኬገን የወግ አጣባቂዎቹን ዳኞች ውሳኔ አጥብቀው የተቃወሙ ሲሆን "ይህ የዛሬው ውሳኔ በርግጠኝነት አንድ ውጤት ይኖረዋል። ያም ሴቶችን በዜግነት የሚገባቸውን ነጻነት እና ዕኩልነት የሚገፍፋቸው መሆኑ ነው።' ብለዋል።

XS
SM
MD
LG