ምሥራቅ ኮንጎ ውስጥ ታጣቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት ደፍረዋል፡፡ ከአሁን ቀደም ባልታየ ደረጃ ብዛት ያላቸውን ልጆች በተዋጊነት መልምለዋል ሲል ዩኒሴፍ አስታወቀ፡፡ በማዕድን ሐብት በከበረው በዚያ የኮንጎ አካባቢ በቅርብ ሳምንታት ውጊያው አየተባባሰ የሄደ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡
የዩኒሴፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ ካትሪን ረስል ባወጡት መግለጫ "በሰሜን እና ደቡብ ኪቩ ግዛቶች በግጭቱ በሚሳተፉት ወገኖች በሕጻናት ላይ ዘግናኝ ጥቃት እየደረሰ መኾኑን ሪፖርት እየደረሰን ነው ብለው በቅርብ ዓመታት ካየነው ሁሉ እጅግ የከፋ መደፈር አና ሌላም ወሲባዊ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም አንዲት እናት "ምግብ ፍለጋ ሲዘዋወሩ የነበሩ ታጣቂዎች የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ስድስት ሴቶች ልጆቻቸውን እንደደፈሩባቸው ለባልደረቦቻችን በዝርዝር ነግረዋል" ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ካለፈው ጥር 27 እስከ የካቲት ሁለት በነበሩት ቀናት የጤና ጣቢያዎች 572 የመደፈር ጥቃት ሰለባዎችን መቀበላቸው የተገለጸ ሲሆን አሃዙ ከዚያ በፊት በነበረው ሳምንት ከተቀበሏቸው አምስት ዕጥፍ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በጤና ተቋማቱ ከታከሙት ውስጥ አንድ መቶ ሰባው ሕጻናት መሆናቸውን በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ የዩኒሴፍ ተጠሪዋ ሊያን ገቸር ተናግረዋል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ኮንጎ ውስጥ በመንግሥቱ የጦር ሠራዊት እና በኤም 23 ታጣቂዎች የሚደርሱትን መድፈር፡ የዘፈቀደ ግድያ እና ሌሎችም ጥቃቶችን እንደሚመረምር ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡
በጦርነት በሚታመሰው ምሥራቅ ኮንጎ ሲቪሎች ላይ ግድያ፣ መድፈር እና ሌላም ወንጀል በመፈጸም የተከሰሱ 84 የመንግሥቱ ወታደሮች የክስ ሂደት ባለፈው ሳምንት ተጀምሯል፡፡
መድረክ / ፎረም