በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ “አትተባበርም” ፤ የመንግሥታቱ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አጣሪ አካል እንዲቋቋም ወሰነ


በጄኔቫ የመንግሥታቱ ድርጅት ቢሮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ በኢትዮጵያ ላይ ለመከረው የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በርቀት ቪድዮ በቀጥታ ግንኙነት ንግግር ሲያደርጉ /ዓርብ፤ ታኅሣስ 8/2014 ዓ.ም. ፤ ጄኔቫ/
በጄኔቫ የመንግሥታቱ ድርጅት ቢሮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ በኢትዮጵያ ላይ ለመከረው የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በርቀት ቪድዮ በቀጥታ ግንኙነት ንግግር ሲያደርጉ /ዓርብ፤ ታኅሣስ 8/2014 ዓ.ም. ፤ ጄኔቫ/

“ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው እጅግ የከበደ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ለመነጋገር” በሚል ዛሬ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አጣሪ አካል እንዲቋቋም ወስኗል። የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ የአፍሪካ ሃገሮች የድጋፍ ድምፅ የሰጠ የለም። የስብሰባውን መጠራት ቀደም ሲልም የተቃወመችው ኢትዮጵያ የምክር ቤቱን አድራጎት “በሉዓላዊነቷ ጣልቃ መግባት” መሆኑን በመግለፅ ኮንና “እንደማትተባበር” አስታውቃለች።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው እጅግ የከበደ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ለመነጋገር” በሚል ዛሬ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አጣሪ አካል እንዲቋቋም ወስኗል። የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ የአፍሪካ ሃገሮች የድጋፍ ድምፅ የሰጠ የለም።

የስብሰባውን መጠራት ቀደም ሲልም የተቃወመችው ኢትዮጵያ የምክር ቤቱን አድራጎት “በሉዓላዊነቷ ጣልቃ መግባት” መሆኑን በመግለፅ ኮንና “እንደማትተባበር” አስታውቃለች።

ስብሰባው እንዲካሄድ የተጠራው በአውሮፓ ኅብረት መሆኑና ከ47ቱ የምክር ቤቱ አባል ሃገሮች አንድ ሦስተኛው ጥሪውን በመደገፋቸው ምክር ቤቱ መሰብሰቡን በምክር ቤቱ ዌብሳይት ላይ የወጣው ፅሁፍ ጠቁሟል።

ለ13 ወራት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ትግራይ ክልል ውስጥ ከአሥር ሰው ዘጠኙ እርዳታ ጠባቂ መሆኑ ለጉባዔው መነገሩንና “በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ አቅርቦቶች ሠራተኞች ባለፈው ሰኔ የማንቂያ ጥሪ ከተሰማ ወዲህ ወደ ክልሉ እየገባ ያለው እርዳታ እጅግ የተወሰነ መሆኑን” የተናገሩት የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ምክትል ከፍተኛ ኮሚሽነር ናዳ አል-ናሺፍ በአሁኑ ጊዜ “ከአራት መቶ ሺህ በላይ የሚሆን ሰው የረሃብ ቸነፈር በሚመስል ሁኔታ ላይ ሳይገኝ አይቀርም” ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል።

ተዋጊዎቹ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ የሚርቀቡላቸውን ዓለም አቀፍ ጥሪዎች እንዲያከብሩ ምክትል ኮሚሽነሯ ጠይቀው ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ውስጥ ቁጥሩ ቢያንስ ሁለት ሚሊየን የሚሆን ሰው መፈናቀሉንና ብዙዎቹ ህይወት አድን እርዳታ እየደረሰላቸው አለመሆኑን መጠቆማቸውን የምክር ቤቱ ዘገባ ጠቁሟል።

ዘገባው ቀጥሎም ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም. ከወጣው ብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወዲህ ‘ህወሓትን ይደግፋሉ’ የተባሉ ‘ከአምስት ሺህ እስከ ሰባት ሺህ የሚሆኑ’ ሰዎች ‘በገፍ መታሠራቸውን’ ከመካከላቸውም ከአሥር በላይ ጋዜጠኞችና የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች እንደሚገኙባቸው፤ ብዙዎቹ ‘ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳይገናኙ መደረጉን ወይም በኃይል ደብዛ ማጥፋት ሊባል በሚችልና ብርቱ ሥጋት በሚያጭር ሁኔታ ያሉበት ቦታ እንዳይታወቅ መደረጉን’ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮው ኃላፊ መናገራቸውን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ‘ፍትኃዊና ነፃ የፍርድ ሂደት እንዲያከናውን’ የጠየቁት ሚስ አል-ናሺፍ ‘ዓለም አቀፍ አሠራር መዘርጋት ተጨማሪ እገዛ ሊሆን እንደሚችል’ አሳስበዋል።

ሁሉም ወገኖች በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አማካይነትና በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ጥረት ‘ትርጉም ላለውና አቃፊ ለሆነ ንግግር እንዲቀመጡ' ምክትል ከፍተኛ ኮሚሽነሯ ጥሪ አድርገዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓለም አቀፍ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም የወሰነው በ21 የድጋፍ፤ በ15 የተቃውሞ ድምፆችና በ11 ተዓቅቦ ሲሆን የጉባዔው አባል ከሆኑ 13 የአፍሪካ ሃገሮች የድጋፍ ድምፅ የሰጠ ማንም የለም። ሰባቱ ተቃውመዋል፤ ስድስቱ ድምፅ ከመስጠት ታቅበዋል።

የ47ቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሃገሮች ድምፆች አሰላለፍ - ከምክር ቤቱ የትዊተር ገፅ የተወሰደ
የ47ቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሃገሮች ድምፆች አሰላለፍ - ከምክር ቤቱ የትዊተር ገፅ የተወሰደ

በውሣኔ ሃሳቡ መሠረት የፊታችን ሰኔ ለሚካሄደው የምክር ቤቱ ሃምሳኛ ጉባዔ ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚጠበቅበት ይህ መርማሪ አካል በምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የሚሰየሙ ሦስት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ባለሙያዎች የሚኖሩት ሲሆን ዕድሜው ሊራዘም የሚችል ሆኖ ለአንድ ዓመት የሚቆይ እንደሚሆን ተዘግቧል።

የቡድኑ ሥራ ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ግጭት በሁሉም ወገኖች ተፈፅመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊና የስደተኛ ህግ ጥሰቶች ውንጀላዎችና አቤቱታዎች ላይ ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተካሄደው ጥምር ምርመራ ላይ ተጨማሪ እንደሚሆንም ዘገባው አመልክቶ ‘ለመርማሪዎቹ የተሰጠው ኃላፊነት በተጠያቂነት፣ በእርቅና ቁርሾን በማሻር ሥራዎች ላይ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ፍትኅ መመሪያ ማሰናዳትን እንደሚያጠቃልል’ ተገልጿል።

በዛሬው ስብሰባው ላይ የኢትዮጵያን አቋም የተናገሩት ጄኔቫ በሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት ቢሮ የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪና በስዊትዘርላንድ፣ በኦስትሪያ፣ በሃንጋሪና በሮማንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነበ ዘገየ ሃገራቸው ለሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ ያላት ቁርጠኛነት ያልተቆጠበ መሆኑን ተናግረው የምክር ቤቱን ስብሰባ “የፖለቲካ ዓላማ ያለው ጣልቃ ገብነት” ብለውታል። እርሳቸው የሚመሩት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንም ሂደቱን እንደሚቃወም ተናግረዋል።

የጉባዔውን ውሣኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋ ባወጣው መግለጫ “የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ በድጋሚ የአንዳንዶች በፖለቲካ የተነሳሳ አጀንዳ ማራመጃነት መጠቀሚያ መሆኑን በመታዘቧ ኢትዮጵያ በእጅጉ አዝናለች” ብሏል።

ምክር ቤቱ ልዩ ጉባዔውን የጠራው “ስብሰባ ከመጥራት ይልቅ ገንቢ በሆነ ሁኔታ እንዲገባና ጉዳዩ ከሚመለከታት ሃገር ጋር በመተባበር መንፈስ እንዲሠራ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀረበለትን ጥያቄ በመግፋት” መሆኑን አመልክቶ “አንዳንዶች በምክር ቤቱ ውስጥ አብላጫ ድምፅ በማግኘት የፈለጉትን ዓላማ ለማሳካት ችለዋል” ብሏል።

ሚኒስቴሩ በመቀጠልም “ይህ የተደረገው ጥምር የምርመራ ቡድኑ ያቀረባቸውን ሃሳቦች ተግባራዊነትና የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይልን ሥራ ያለማወላወል እንዲደግፉ፣ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ የሚያካሂዷቸውን ምርመራዎች ወደፊትም እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና ለምክር ቤቱ አባላት ሁሉ ታኅሣስ 5/2014 ዓ.ም. ያስገባውን ጥያቄ በሚፃረር ሁኔታ ነው” ብሏል።

“ይህ ምክር ቤቱ ውስጥ ባሉ አንዳንዶች የተፈፀመ አድራጎት - ይላል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ በማስከተል - በሉዓላዊት ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት አማራጭ ለመፈለግ የተደረገ ሙከራ ነው፤ በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ ከማባባስ በስተቀር የሚፈይደው አንዳች ዓላማ የለውም።”

በምክር ቤቱ አማካይነት ‘ተቋማትን (አሠራሮችን) የማበራከት ልማድ በብዙ አጋጣሚዎች ግባቸውን ሳይመቱ የከሸፈ’ መሆኑን መግለጫው አመልክቶ “በውስጥ ጉዳዮቻቸው ጣልቃ መግባትን በማይቀበሉ ሃገሮች ላይ ጫና ማሳረፊያ መሣሪያ ብቻ ሆነዋል” ብሏል።

ኢትዮጵያ ልዩ ስብሰባውንና “በፖለቲካ የተነሳሳ፣ በምክር ቤቱ ሥራ ላይ እምነት የሚያሳጣ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የግዛት ጥብቅነቷን፣ ብሄራዊ ልዕልናዋንና የፖለቲካ ነፃነቷን የሚዳፈር” ሲል የፈረጀውን ውጤት “ጨርሶ አትቀበልም” ብሏል መግለጫው።

“ኢትዮጵያ ያለዕውቅናዋ ከተጫነባት ከዚህ ከተፈጠረ አሠራር (ተቋም) ጋር እንደማትተባበር በድጋሚ ታረጋግጣለች” ብሏል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ። “ድጋፋቸውን የገለፁላትንና አብረዋት የቆሙትን” እንደምታመሰግንና “በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ሰብዓዊ መብቶችን በማክበርና በመጠበቅ ቁርጠኛነቷ እንደምትገፋ” አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የተዘጋው “መንታ አቋም ይበቃል፤ የአንድ ወገን በጉልበት የማዋከብ እርምጃዎችን መውሰድ ይበቃል፤ በሰብዓዊ መብቶች ስም በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ መግባት ይበቃል” በሚሉ መልዕክቶች ነው።

በሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ለምርመራ ኮሚሽኑ መቋቋም የድጋፍ ድምፅ የሰጡት አርጀንቲና፣ አርሜንያ፣ ኦስትሪያ፣ ባሃማስ፣ ብራዚል፣ ቡልጋሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ፊጂ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ኢጣልያ፣ ጃፓን፣ ማርሻል ደሴቶች፣ ሜክሲኮ፣ ሆላንድ፣ ፖላንድ፣ ደቡብ ኮሬያ፣ ዩክሬን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩሩጓይ ሲሆኑ የተቃወሙት ደግሞ ቦሊቭያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካመሩን፣ ቻይና፣ ኮት ዲ’ቯር፣ ክዩባ፣ ኤርትራ፣ ጋቦን፣ ሕንድ፣ ናሚብያ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ፣ የሩስያ ፌደሬሽን፣ ሶማሊያ፣ ቬኔዝዌላ ናቸው። ባህሬን፣ ባንግላዴሽ ኢንዶኔዥያ፣ ሊብያ፣ ማላዊ፣ ሞሪታኒያ፣ ኔፓል፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን፣ ቶጎና ኡዝቤክስታን ድምፅ ከመስጠት ታቅበዋል።

XS
SM
MD
LG