ባለፈው ዓመት ብቻ በዓለም ላይ 89.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በጦርነት፣ ጥቃት እና የስብዓዊ መብት ረገጣ ምክንያት ከሀገራቸው ተገፍተው ወጥተዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ወኪል ዛሬ አስታውቋል።
ይህም ብዛት ከዚህ በፊት ያልታየ ነው ሲል የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጣው ዓመታዊ የዓለም አዝማሚያ ሪፖርት ላይ ጠቅሷል።
የተመድ የስደትኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ፊሊፖ ግራንዲ እንደሚሉት ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ሲጨመርበት አጠቃላይ ድምሩ ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን ይችላል።
“ከዩክሬን የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከ12 እስከ 14 ሚሊዮን ሲገመት አጠቃላይ ድምሩ ከ100 ሚሊዮን በላይ ይሆናል ማለት ነው፥ የህም በግጭትና ቀውስ መጨመር ምክንያት ነው” ብለዋል ግራንዲ።
ድንገተኛ አደጋዎችና ችግሮች ባለፈው 10ት ዓመታት የስደተኞችን ቁጥር ከፍ እንዲል አድርገዋል። የተመድ የስደተኞች ጉዳይ መስሪያቤት እንደሚለው የሩሲያ ዩክሬንን መውረር ቁጥሩን በከፍተኛ ብዛትና ፍጥነትና አሳድጎታል። ይህም ከሁለተኛው የየዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛውና ፈጣኑ መፈናቀል መሆኑ ነው።
የቪኦኤዋ ሊሳ ሽላይን ከጄኔቫ በላከችው ዘገባ መሰረት፣ የዓለም ትኩረት ዩክሬን ላይ በሆነበት ስዓት፥ ፊሊፖ ግራንዲ እንዳሳሰቡት፣ መንግሥታት ከዩክሬን በፊት ተፈጥረው በነበሩና የሚሊዮኖችን ህይወት ባመሳቀሉ ችግሮች ላይም ትኩረት ማድረግ አለባቸው።
“በ2020 መጨረሻ ኢትዮጵያ፣ ባለፈው በጋ ደግሞ አፍጋኒስታን፥ ሶሪያና ደቡብ ሱዳን፣ የፍልስጤም ስደተኞች ጉዳይየመሳሰሉት ነባርና ቁጥሩን ከፍ የሚያደርጉ ቀውሶች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል ግራንዲ።
የስደተኞች ጉዳይ ቢሮው እንደሚለው ባለፈው ዓመት ጥገኝነት ያገኙት ሰዎች ቁጥር 27 ሚሊዮን ሲደርስ በገዛ ሀገራቸው ውስጥ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉት ደግሞ 53.2 ሚሊዮን ደርሷል። ኮሚሽኑ እንዳለው ከሚታመነው በተቃራኒ 80 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች የሄዱት ወደ ደሀና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገሮች ነው።
ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው አምስት ሀገሮች ሶሪያ፣ ቬንዝዌላ፣ አፍጋኒስታን፣ ደቡብ ሱዳን እና ማይናማር ከሦስት እጅ በላይ የሚሆኑት ስደተኞች መነሻ ናቸው። ቱርክ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኛ ስታስተናግድ፥ ኮሎምቢያ ዩጋንዳ፡ ፓኪስታን እና ጀርመን ይከተላሉ።
አሜሪካ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ማረፊያ በመሆን በዓለም ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘች ነው።