በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ የዩክሬን ጉዳይ ትልቁን ሥፍራ ይይዛል


በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ የዩክሬን ጉዳይ ትልቁን ሥፍራ ይይዛል
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:56 0:00

የዓለም መሪዎች የሚሰባሰቡበት የዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የሚካሄደው የዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ቀብር ጥላውን ባጠላበትና ፣ የዩክሬን ጦርነት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ሊደርስ ይችላል በተባለበት በዚህ ወቅት ነው፡፡

መስከረም 9/ 2015 ዓ.ም የሚካሄደው የዳግማዊት ንግሥት ኤልባዜጥ ቀብር በ77ኛ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለሚገኙት መሪዎች የፕሮግራም መጨናነቅ ፈጥሯል፡፡

በንግሥቲቱ ቀብር ላይ የሚገኙ መሪዎች ከለንደን ወደ ኒው ዮርክ ጉዞ ላይ ሊሆኑ ስለሚችሉም የአንዳንዶቹ ንግግሮችና ስብሰባዎች መርሃ ግብር መቀየር ሊኖርበት ይችላል፡፡

የዘንድሮው ጉባዔ የሚካሄደው “ትልቅ አደጋ ላይ ባለንበት በዚህ ወቅት ነው” የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ

“ዓለማችን በጦርነት ተመሰቃቅላለች፣ በአየር ንብረት ቀውስ በተደጋጋሚ ተመታለች፣ በጥላቻ ተጎድታለች፣ በድህነት፣ በረሀብና እኩልነት እጦት ተሸማቃለች፡፡” ብለዋል፡፡

ምናልባት ወሳኝ ወታደራዊ ውጤት ሊታይበት ይችላል የተባለው ሩሲያ ዩክሬን ላይ የምታካሂደው ጦርነት በዓመታዊ ጉባዔው ላይ ትልቁን ሥፍራ መያዙ አይቀርም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የጦሩነቱን ወቅታዊ ለመገምገም ዛሬ ሀሙስ እንደሚሰበሰብ ተገልጿል፡፡

በዛፖሮዥዢያ የኒውክለር ማብለያ ተቋም ያለው ሁኔታ የተለየ ትኩረት እንደሚያገኝም ተመልክቷል፡፡

ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ድሬክተር ይህን አስመልክቶ ሲናገሩ

“በእሳት እየተጫወትን ነው፡፡ ከኒውክለር አደጋ አንዲት ስንዝር ርቀት ላይ በሆንበት ሁኔታ ልንቀጥልን አንችልም፡፡ የዛፖሮዥዢያ ኒውክለር ማብለያ ተቋም ደህንነት ቋፍ ላይ ነው ያለው፡፡” ብለዋል፡፡

ምዕራባውያን ባለሥልጣናት በበኩላቸው ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ እያወላወሉ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ አገሮች ድጋፋቸው የበለጠ እንዲጠናከር ይፈልጋሉ፡፡

ሪቻርድ ጎዋን በዓለም አቀፉ የቀውስ ተከታታይ ቡድን የተባበሩት መንግሥታት ክፍል ዋና ዳይሬከተር ናቸው፡፡

“ብዙዎች የአፍሪካና እስያ አገሮች ከሩሲያ ጋር የደህንነት ወይም የኢኮኖሚ ግንኙነት አላቸው፡፡ መጋቢት ላይ ወረራውን ለመንቀፍ ፈቃደኞች የነበሩ ቢሆንም በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ከሞስኮ ጸብ ውስጥ መግባትን ለመቀጠል አይፈልጉም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፊትም ቢሆን አልፎ አልፎ የሚገኙት የሩሲያ ፕዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዘንድሮው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ አይገኙም፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪም ይገኙ እንደሆን በእርግጠኛንነት አይታወቅም፡፡ እናም በጉባዔው ላይ ጦርነቱን አስመልክቶ ትልቅ ውጤት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ “አሁን ባለው ሁኔታ የሰላም ሥምምነት ላይ የሚደርሱበት ዕድል እጅግ አነስተኛ ነው እዚያ ላይ ምንም ብዥታ የለኝም ፡፡” ብለዋል፡፡

ሩሲያና ዩክሬን ዋነኞቹ የምግብ አምራች ሀገሮች ስለሆኑ ጦርነቱ የዓለም ምግብ ቀውስን አባብሷል፡፡

የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥና የምግብ ዋጋ መናር በ40 ዓመት ውስጥ ለከፋው ድርቅ በመጋለጥ ላይ ያለውን የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ እንዲባባስ አድርጓል።

እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለከባድ የረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ የረሃብ ቸነፈር በሶማልያ ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ላይ እያንዣበበ ነው፡፡

በሶማልያ የድርቁ ምላሽ ልዩ መልዕከተኛ አብዲራህማን አብዲሻኩር “የረሀቡ ቸነፈር እውነት ነው፣ እየደረሰ እየሆነም ነው፡፡” ይላሉ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ችግሩን ለመቅረፍ ከሚካሄዱት በርካታ ስብሰባዎች አእንዱ የሆነውን ከፍተኛ የዓለም አእቀፍ የምግብ ዋስትና ጉባኤ ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

XS
SM
MD
LG