በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ግጭት በብሔራዊ የጤና ቤተ ሙከራ ደኅንነት ላይ ስጋት ደቅኗል


የሱዳን ግጭት በብሔራዊ የጤና ቤተ ሙከራ ደኅንነት ላይ ስጋት ደቅኗል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:32 0:00

የሱዳን ግጭት በብሔራዊ የጤና ቤተ ሙከራ ደኅንነት ላይ ስጋት ደቅኗል

በሱዳን ግጭት ውስጥ ከገቡት ወገኖች አንዱ፣ በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚገኘውንና ለሥነ ሕይወት(ባዮሎጂካል) ምርምር የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን የያዘውን ብሔራዊ የጤና ቤተ ሙከራ መቆጣጠሩን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ያስታወቁ ሲኾን፣ ድርጊቱ “እጅግ አደገኛ” እንደኾነ በይነዋል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ፣ ከሀገር የሚሰደዱ ሱዳናውያን ቁጥር እያሻቀበ መሔዱንም ተቋሙ አስታውቋል።

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የሚገኘው ብሔራዊ የጤና ቤተ ሙከራ፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ከሱዳን ተዋጊዎች መካከል በአንዱ ቡድን ቁጥጥር ሥር መዋሉ ይፋ የተደረገው፥ በሁለቱ የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች መካከል፣ አጣብቂኝ ውስጥ የሰነበቱ ሱዳናውያን፣ ከአካባቢው መሸሻቸውን እንደሚቀጥሉ ባለሥልጣናት እያስጠነቀቁ ባሉበት ወቅት ነው፡፡

ውጊያው ሱዳንን ወደ ትርምስ የከተታት ሲኾን፣ ቀድሞውንም በከፍተኛ ርዳታ የምትተዳደረውን አፍሪካዊት ሀገር ወደ ውድቀት አፋፍ አድርሷታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከግጭቱ በፊት፣ የሱዳን አንድ ሦስተኛ ሕዝብ ወይም 16 ሚሊየን የሚኾነው ወገን፣ ርዳታ ፈላጊ ነበር። አሁን ደግሞ ቁጥሩ ይጨምራል።

በሱዳን የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ኒማ ሰዒድ አቢድ፣ “ከተዋጊ ወገኖች አንዱ” ሲሉ የትኛው እንደኾነ በውል ያለዩት ቡድን፣ በካርቱም የሚገኘውን ማዕከላዊ የሕዝብ ጤና ቤተ ሙከራ መቆጣጠሩንና በውስጡ ይሠሩ የነበሩትን ባለሞያዎች(ቴክኒሺያኖች) ማስወጣታቸውን ገልጸዋል።

አቢድ፣ በጄኔቫ በተካሔደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ ላይ፣ ከፖርት ሱዳን በቪዲዮ ተገኝተው ስለ ኹኔታው ሲያብራሩ፣ “እጅግ፣ እጅግ አደገኛ ነው፤” ያሉ ሲኾን፣ በቤተ ሙከራው ውስጥ የፖሊዮ፣ የኩፍኝ እና የኮሌራ ቫይረስ እንደሚገኙ ገልጸዋል። አቢድ አክለውም፣ “ካርቱም የሚገኘው ማዕከላዊ የሕዝብ ጤና ቤተ ሙከራ፣ ከተፋላሚ ወገኖች በአንዱ መያዙ፣ አስከፊ የሥነ ሕይወት አደጋ ስጋት ደቅኗል፤” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ኹኔታውን አስመልክቶ፣ የዓለም ጤና ድርጅት በአወጣው መግለጫ፣ የቤተ ሙከራው ባለሞያዎች መባረራቸው እና በካርቱም የደረሰው የኃይል መቋረጥ፣ በቤተ ሙከራው ውስጥ ለሕክምና አገልግሎት ተብለው የተቀመጡትን የሥነ ሕይወት ቁሳቁሶች በአግባቡ መቆጣጠር እንደማይቻል የሚያሳይ መኾኑን አመልክቷል፡፡

ቤተ ሙከራው የሚገኝበት ማዕከላዊ ካርቱም፥ የሱዳን ብሔራዊ ጦር፣ ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ከሚባሉትና በዳርፉር ግጭት በተፈጸመው አሠቃቂ ድርጊት መሳተፋቸው ከሚገለጸው የጃንጃዊድ ሚሊሺያዎች የተወጣጣው ቡድን ጋራ፣ ውጊያ ከሚያካሒድበት አቅራቢያ ነው።

ውጊያው ከተቀሰቀሰበት እ.አ.አ. ሚያዝያ 15 ቀን ጀምሮ፣ ቢያንስ 20 ሺሕ ሱዳናውያን ወደ ቻድ ተሰድደዋል። በሱዳን ይኖሩ የነበሩ አራት ሺሕ የሚኾኑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችም፣ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር(ዩኤንኤችሲአር) ቃል አቀባይ ኦልጋ ሳራዶ ተናግረዋል።

የስደተኞች ቁጥር፣ ከዚኽም በላይ እንደሚያሻቅብ ያስጠነቀቁት ሳራዶ፣ ወደ ሌሎች አምስት የሱዳን አጎራባች ሀገሮች የተሰደዱ ሱዳናውያን አኀዝ እንደሌላቸው ገልጸዋል። ዩኤንኤችሲአር፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች፣ ከሱዳን ሸሽተው ግብጽ መግባታቸውን አመልክቷል።

የሱዳን እና የግብፅ ድንበር፣ ከሱዳን ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎችን በሚያመላልሱ አውቶቡሶች ተጨናንቋል፤ የሚሸሹ ሰዎችም ድንበሩን አቋርጠው ወደ ሱዳን ለመግባት ተሰልፈው ሲጠብቁ ይታያሉ። አሕመድ ኤልባድዌይ፥ ተሰልፈው ከሚጠብቁት ሰዎች መሀል ሲኾን፣ “ወደ ሱዳን ድንበር ከደረስኹ ከ14 ሰዓታት በላይ ኾኖኛል። ድንበሩ ከትላንት ምሽት ጀምሮ ተዘግቷል፡፡ ስለዚኽ መሻገር አልቻልንም። እዚኽ ምግብም ኾነ ውኃ የለም። እህል ከቀመስኹ ሁለት ቀን ኾኖኛል፤” ሲል ተናግሯል፡፡

ኤልባድዌይ አያይዞም፣ “ድንበሩ ማታ ማታ ይዘጋል። ጠዋት ብቻ ነው የሚከፈተው። አሁን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ኾኗል፤ ነገር ግን እስከ አሁን አልተከፈተም። ድንበሩ እስኪከፈት እና ፓስፖርቴ ላይ ማኅተም ተደርጎበት እስክሻገር እየጠበቅኹ ነው፤” ሲል፣ ድንበሩ ተከፍቶ ወደ ግብጽ ለመሻገር ያለውን ጉጉት ገልጿል።

ግጭቱ፣ ተጨማሪ መፈናቀሎችን በሀገር ውስጥም በውጭም እንደሚያስከትል ያመለከቱት የዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ፣ የውጭ መንግሥታት የኤምባሲ ሠራተኞቻቸውንና ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት እየተሯሯጡ ባሉበት ወቅት፣ ድርጅቱ ሥራውን ለማስፋፋት እና ለማጠናከር እየጣረ መኾኑን አመልክቷል።

ከ800 ሺሕ በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች በሱዳን የሚኖሩ ሲኾኑ፣ ከእኒኽም ሩቡ በካርቱም ዋና ከተማ የሚገኙ በመኾናቸው፣ በግጭቱ ቀጥተኛ ተጎጂ ኾነዋል። በአጠቃላይ ሱዳን፣ 1ነጥብ1 ሚሊዮን ስደተኞችን የምታስተናግድ አገር ስትኾን፣ በብዛት ከዳርፉር የተፈናቀሉ 3ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም አሏት።

በተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ ድርጅት ምልከታ መሠረት፣ በሱዳን የሚካሔደው ግጭት፣ በመጪዎቹ ሳምንታት ውስጥ ይወልዳሉ ተብለው የሚጠበቁ 24 ሺሕ ሴቶችን ጨምሮ፣ በ10 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ነፍሰ ጡር እናቶችን ያሰጋል።

በመላ አገሪቱ የሚገኙ 219ሺሕ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ውጊያው፣ እየተካሔደ ባለበት ወቅት፣ ከቤታቸው ወጥተው ወደ ሆስፒታሎች እና ክሊኒኮች መሔድና አስቸኳይ ርዳታ ማግኘት አደገኛ እንደሚኾንባቸው ተቋሙ ጨምሮ ገልጿል።

በሱዳን፥ በርዳታ ሠራተኞች፣ በሰብአዊ ተቋማት እና በመጋዘኖቻቸው ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ሌሎች የረድኤት ተቋማትም በሱዳን ያደርጉት የነበረውን የርዳታ ሥራ ለማቆም ወይም ለመቀነስ ተገድደዋል፡፡

ከሚያዚያ 15 ቀን ወዲህ፣ ሦስት የዓለም ምግብ ድርጅት ሠራተኞችን ጨምሮ ቢያንስ አምስት የርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል።

XS
SM
MD
LG