በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ ለሚቀጥለው ዓመት ከፍተኛውን የ51.5 ቢሊዮን ዶላር የነፍስ አድን እርዳታ ጠየቀ


ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ኦቻ) ኃላፊ ማርቲን ግፍሪትስ
ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ኦቻ) ኃላፊ ማርቲን ግፍሪትስ

የተባበሩት መንግሥታትና አጋሮቹ እአአ በ2023 የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በአስር ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች እስከዛሬ ከፍተኛ የሆነውን የ51.5 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ግምገማ በሚቀጥለው ዓመት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ65 ሚሊዮን በላይ ተጨማሪ ሰዎች እንደሚኖሩ የገመተ ሲሆን፣ ይህም በ68 አገሮች ውስጥ ያሉትን ተረጂዎች ቁጥር ወደ 339 ሚሊዮን እንደሚያደርሰው ተገልጿል፡፡

ያ ቁጥር ከዓለም 4 ከመቶ ወይም የዩናይትድ ስቴትስን ህዝብ ብዛት ያህል እንደሚሆን በዘገባው ተመልክቷል፡፡

“ስለሆነም የሚቀጥለው ዓመት በዓለም ትልቁ የሰብአዊነት መርኃ ግብር የሚካሄድበት ነው” ሲሉ ትናት በሰጡት መግለጫ የተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ኦቻ) ኃላፊ ማርቲን ግፍሪትስ፣ የዩክሬን ጦርነትና የአፍሪካ ቀንድ ድርቅን አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም ላይ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ግጭትና የአየር ንብረት ለውጥ ከቤታቸው እንዲሰደዱ በማድረግ የተፈናቃይነት ቀውስ ማስከተሉም በሮይተርስ ዘገባ ተመልክቷል፡፡

9 ወራት ያስቆጠረው የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት የምግብ አቅርቦትን ያቃወሰ በመሆኑ በ37 አገሮች የሚገኙ 45 ሚሊዮን ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸው ተነግሯል፡፡

በዚህ ዓመት የተጠየቀው የእርዳታ ገንዘብ ከአምናው በ25 ከመቶ መጨመሩም ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ለጋሾች በበርካታ ጫና ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስካዛሬ ገጥሞት የማያውቀውን ክፍተት መፈጠሩ ተነግሯል፡፡

ተመድ እአአ በ2022 ከጠየቀው ማግኘት የቻለው የገንዘብ ድጋፍ 53 ከመቶ ብቻ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

“የተፈጠረው ክፍተት በፈላጊው ቁጥር ማደግ እንጂ በገንዘብ እጥረት አይደለም” ያሉት ማርቲን ግሪፍትስ “በዩክሬን ባለው ጦርነት፣ በኮቪድ-19፣ በአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት ፍላጎቶች እየጨመሩ ነው፡፡ በሚቀጥለው የ2023 እነዚህ ሁሉ የመጨመር አዝማሚያ ያሳያሉ ብዬ እሰጋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG