በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራውያን በብሔራዊ አገልግሎት ወቅት ሥቅየት እና ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው የተመድ መርማሪ አስታወቀ


ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ በአስገዳጅ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ወቅት፥ ሥቅየት፣ ኢሰብአዊ እና አዋራጅ አያያዝ፣ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ የግዳጅ ሥራ እና በደል እንደደረሰባቸው መናገራቸውን፣ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች መርማሪ፣ ትላንት ሰኞ በተሰራጨ ሪፖርት ላይ አስታወቁ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች መርማሪ ሞሐመድ ባቢከር፣ በሪፖርታቸው ላይ እንዳመለከቱት፣ ኤርትራ የጊዜ ወሰን የሌለው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ፖሊሲ እንዳላት ገልጸው፣ አገልግሎቱ፥ የሲቪል እና ውትድርና አገልግሎቶችን እንደሚጨምር አስታውቀዋል።

ልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት፣ አገሪቱ፥ ለብሔራዊ አገልግሎት ሕጋዊ ገደብ እንድታስቀምጥና የተሳታፊዎችን ሰብአዊ መብቶች እንድታከብር ያቀረቧቸውን በርካታ ጥሪዎች ችላ እንዳለች አብራርተዋል።

ኤርትራ፣ የብሔራዊ አገልግሎት መርሐ ግብሯ፣ “ፍትሐዊ ባልኾነ መልኩ አስተያየት እንደሚሰጥበት” ስትገልጽ፣ ባቢከር በአንጻሩ፣ “በአስገዳጅ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ስም፣ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ” ፣ ተኣማኒነት ያላቸው በርካታ ሪፖርቶች እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል። በኤርትራ ውስጥ ምንም ዐይነት ተቃውሞ እንደማይፈቀድ ያብራሩት መርማሪው፣ ወታደራዊ አገልግሎቱን ጥለው የሚኮበልሉ ወይም ለማምለጥ የሚሞክሩ ወጣቶች፣ ለዘፈቀደ እስር፣ መሰወር እና ሥቅየት እንደሚዳረጉም አመልክተዋል። የሰብአዊ መብቶች አቀንቃኝ ተቋማት፣ ኤርትራን፥ ከዓለም እጅግ ጨቋኝ አገሮች አንዷ አድርገው እንደሚገልጿት ያመለከተው አሶሺዬትድ ፕሬስ፣ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ነፃነቷን ከተቀዳጀችበት ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በፊት አንሥቶ፣ ምንም ዐይነት ምርጫ አካሒደው በማያውቁት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ እንደምትመራ አስታውሷል።

ልዩ መርማሪው፣ ከኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ብዙኀኑ አገራቸውን ለቀው የሚወጡት፣ በዚኹ ገደብ አልባ እና አስገዳጅ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ምክንያት እንደኾነ መናገራቸውን፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በቀረበው፣ የ12 ወራት ሪፖርት አመልክተዋል።

ሪፖርቱ ይፋ የተደረገው፣ ኤርትራውያን፣ በስቶኮልም ከተማ ዳርቻ ያካሔዱትን የባህል ፌስቲቫል፣ ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች፣ ከወረሩት እና ወደ ሁከት ከተቀየረ ከቀናት በኋላ ነው፡፡ በዚኹ ሁከት፣ ቢያንስ 52 የሚደርሱ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ የስዊድን ብዙኀን መገናኛ ዘግቧል።

ኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ ጋራ በምትጎራበትበት የትግራይ ክልል፣ “ወታደሮቿን እያስገባች፣ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ታካሒዳለች፤” በሚል ክሥ ይቀርብባታል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG