በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ የርዳታ ምግብ ሥርጭቱን አቋረጠ


የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ የርዳታ ምግብ ሥርጭቱን አቋረጠ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:36 0:00

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ ለረኀብ ለተጋለጡ ሰዎች በተለገሰ የርዳታ ምግብ ላይ የተፈጸመውን ምዝበራ ለማጣራት የያዘውን የውስጥ ምርመራ እያካሔደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የሚያካሒደውን የርዳታ ምግብ ሥርጭት ማቋረጡን፣ አራት የረድኤት ሠራተኞች አስታወቁ።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ከሌሎች አጋሮቹ የተገኘውን የርዳታ ምግብ፣ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና ባለፈው ጥቅምት ወር መገባደጃ በሰላም ስምምነት የቆመው አስከፊ ጦርነት አንዷ ማዕከል ወደነበረችው ትግራይ የማድረስ ሓላፊነት ወስዶ በመሥራት ላይ ነበር።

እንደ መንግሥታቱ ድርጅት አኀዛዊ መረጃ፣ ብዛቱ ስድስት ሚሊዮን እንደሚኾን ከሚገመተው የክልሉ ሕዝብ፣ ከአምስት ሚሊየን በላይ የሚኾነው፣ የምግብ ርዳታ ፈላጊ ነው።

“ያለሙ የምግብ ፕሮግራም፣ ለትግራይ የሚላከው የርዳታ ምግብ ከታለመለት ዓላማ ውጭ መዋሉን ተከትሎ፣ ባለፈው ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የምግብ ዕደላውን ለጊዜው ማቋረጡን፣ ለሰብአዊ አጋሮቹ አስታውቋል፤” ሲሉ፣ ከአራቱ የረድኤት ሠራተኞች አንዱ ለአሶሽዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል። የተቀሩት ሦስቱም የተባለውን መረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጣቸውን፣ የዜና ወኪሉ አክሎ ዘግቧል። ይኹንና ጉዳዩን አስመልክቶ፣ ለብዙኃን መገናኛ መረጃ የመስጠት ፈቃድ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ አራቱም የረድኤት ሠራተኞች ስማቸው ይፋ እንዳይደረግ ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም(WFP)፣ አጠቃላይ ቁጥሩ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ፣ በድርቅ እና ግጭቶች ሳቢያ፣ ሰብአዊ ረድኤት በሚሻባት ኢትዮጵያ፣ ከታለመለት ዓላማ ውጭ በዋለውና

ዝርፊያ በተፈጸመበት የርዳታ ምግብ ጉዳይ፣ ምርመራ እያካሔደ መኾኑን፣ አሶሽዬትድ ፕሬስ ባለፈው ወር ባወጣው የዜና ዘገባ ይፋ አድርጎ ነበር።

የዓለሙ የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቢሮ ዲሬክተር፣ ባለፈው መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የረድኤት ሥራ አጋሮቻቸው በላኩት ደብዳቤ፥ ከዓላማው ውጭ ስለዋለውና ዝርፊያ ስለተፈጸመበት የርዳታ ምግብ ጉዳይ “የምታውቁት ነገር ካለ፤ ሠራተኞቻችኹ ወይም ተረጂዎቻችኹ አልያም የአካባቢው ባለሥልጣናት ያደረሷችኹ መረጃዎች ካሉ አጋሩን፤” ማለታቸው ተዘግቦ ነበር።

“የተዘረፈው የምግብ መጠን፣ አንድ መቶ ሺሕ ያህል ሰዎችን ለመመገብ የሚያስችል ነው፤” ሲሉ፣ ሁለት የርዳታ ሠራተኞች፣ በወቅቱ ለአሶሽዬትድ ፕሬስ መናገራቸው ይታወሳል። የርዳታ ምግቡ ተከማችቶ ከነበረበት፣ በሽራሮ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ አንድ የምግብ ማከማቻ መጋዘን ነው የተዘረፈው። ለዝርፊያው ተጠያቂው ማን እንደኾነ ግን፣ በጊዜው አልታወቀም።

በሌላ በኩል፣ ዐዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የርዳታ እህልን ከዓላማው ውጭ የማዋል እና ለገበያ የማውጣት ድርጊት እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በዚኹም ጉዳይ ላይ፣ ባለፈው ወር፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ መቐለን በጎበኙበት ወቅት እንደተወያዩበት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG