በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጀርመን ከተሞች የተካሄዱ የሩሲያን ወረራ ደጋፊ እና ተቃዋሚ ሰልፎች


በጀርመን ከተሞች የተካሄዱ የሩሲያን ወረራ ደጋፊ እና ተቃዋሚ ሰልፎች ፍራንክፈርት ጀርመን
በጀርመን ከተሞች የተካሄዱ የሩሲያን ወረራ ደጋፊ እና ተቃዋሚ ሰልፎች ፍራንክፈርት ጀርመን

ትናንት እሁድ ፍራንክፈርት እና ሃኖቨርን በመሳሰሉ የጀርመን ከተሞች ሩሲያን በመደገፍ ከወጡት ሰልፈኞች ዩክሬንን በመደገፍ የወጡት ቁጥር በእጅጉ የበለጠ እንደነበር የከተሞቹ ፖሊሶች ገለጡ።

ሃኖቨር ከተማ ውስጥ ስድስት መቶ የሚሆኑ የሩሲያ ደጋፊዎች የሀገሪቱን ባንዲራ እያውለበለቡ በከተማዋ ጎዳናዎች በመኪና ተከታትለው የተዘዋወሩ ሲሆን በአንጻሩ 3500 የሚሆኑ የዩክሬን ደጋፊዎች መሃል ከተማ አደባባይ ላይ ተሰባስበው ድጋፋቸውን መግለጻቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ፍራንክፈርት ውስጥም ስምንት መቶ የሚሆኑ የሩሲያ ደጋፊዎች እና 2500 የዩክሬን ደጋፊዎች እንደወጡ ነው ፖሊሶች ያመለከቱት።

ደጋፊ እና ተቃዋሚውን በአጥር መለያየታቸውን ፖሊሶቹ ጠቅሰው ሆኖም አልፎ አልፎ ሁለቱ ወገኖች ተፋጥጠው ከመጨቃጨቃቸው በስተቀር ባመዛኙ በሰላማዊ መንገድ ማብቃቱን አመልክተዋል።

ጀርመን ውስጥ እአአ በ2020 በተጠናቀረ መንግሥታዊ አሃዛዊ መረጃ መሰረት ቁጥራቸው ወደሁለት መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ የሚገመቱ የሩስያ ዜጎች ይኖራሉ። ከሩሲያ ወረራ በፊት ጀርመን ይኖሩ የነበሩት ዩክሬይናውያን አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ ይደርሱ እንደነበር መረጃው ያመለክታል። ሆኖም ሩሲያ ወረራ ከከፈተች ወዲህ ሶስት መቶ ሺህ የሚደርሱ ተጨማሪ ዩክሬናውያን ጀርመን ገብተዋል።

ፍራንክፈርት ላይም የከተማዋ ባለስልጣናት በጎዳና ላይ የሚካሄድ የመኪና ላይ ሰልፍ በመከልከላቸው ወደ ስምንት መቶ የሚሆኑ የሩስያ ደጋፊዎች የከተማዋ መሃል አደባባይ ላይ ተሰባስበዋል።

ሁለት ሽህ አምስት መቶ የሚሆኑ የዩክሬን ደጋፊዎች በበኩላቸው በሌሎች የፍራንክፈርት አካባቢዎች "ጦርነት ይቁም" የሚሉ ሰሌዳዎችን አንግበው እና የዩክሬይን ባንዲራ ቀለማት ፊታቸው ላይ ተቀብተው ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ሰልፎቹ ከመካሄዳቸው በፊት የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎች ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳላቸው ገልጸው ሆኖም የሩስያን የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ማስተጋባት እና ወረራውን የመደገፍ ተግባር አንታገስም ማለታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

በፍራንክፈርቱ ሰልፍ ላይ "ዶንባስ የሩስያ ግዛት ነች" የሚሉ መፈክሮች ሲያሰሙ የነበሩ የሩሲያ ደጋፊዎችን ፖሊሶች ሲገስጹ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG