በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች እየተጣሉ ነው


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሉን ይፋ አድርገዋል
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሉን ይፋ አድርገዋል

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ላይ “ያለምንም በቂ ምክንያት ተገቢ ያልሆነ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽማለች” ሲሉ ባወገዟት ሩሲያ ላይ፣ ሌላኛውን ዙር ተጨማሪ ማዕቀብ መጣላቸውን በትናንትናው እለት አስታውቀዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት መሪዎችም፣ ብራስልስ ላይ ትናንትና በአደረጉትና ዛሬ ዓርብም በቀጠለው አስቸኳይ ስብሰባቸው፣ በሩሲያ ላይ መጠነ ሰፊ ያሉትን ማዕቀብ መጣላቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የሩሲያን ባንክ አምስት ዘርፎች የፋይናንስ፣ የኃይል፣ የትራንስፖርት ዘርፍና፣ እንዲሁም የውጭ ንግድ ቁጥጥርና የቪዛ ፖሊሲዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኡርሱላ ቮን ደር ለየን ይህንኑ ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ

“ይህ ጥቅል የማዕቀብ ሰነድ በዋነኝነት ሩሲያን ከአብዛኛው የካፒታል ገበያዎች ያወጣታል፡፡ አሁን 70 ከመቶ የሚሆኑትን የሩሲያ ባንኮችን ገበያ ኢላማ አድርገናል፡፡ በተለይም በመከላከያው ዘርፍ ያሉትን ጨምሮ ቁልፍ የመንግሥት ኩባንያዎችንም ይጨምራል፡፡ ይህ የሩሲያን የብድር ወጪዎች እንዲጨምሩ፣ የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ፣ የሩሲያ ኢንድስትሪዎችም በሂደት እንዲዳከሙ ያደርገዋል፡፡”

የአውሮፓ ህብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት የፈረንሳይ መሪ ኤማኑኤል ማክሮን ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ጋር ትናንት ሀሙስ በስልክ መነጋገራቸው ገልጸዋል

“በዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚየር ዘለነስኪ ጥያቄ መሠረት ከፕሬዚዳንት ፑትን ጋር ግልጽና ቀጥተኛ ንግግር ያደረግኩት ወዲያውኑ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙና ከሁሉም በላይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ዘለነስኪ በጠየቀት መሰረት ከሳቸው ጋር እንዲነጋገሩ ፑትንን ለማግባባት ነበር ግን ያ ሊሆን አልቻለም፡፡

ስለዚህ ይህን ግልጽ መልዕክት ከፈረንሳይ ለሩሲያ ፌደሬሽን አስተላልፌያለሁ ከዩክሬን ፕሬዚዳንትም ወደ ፕቱን የተላለፈውን መልዕክት አድርሻለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን እንደምትመለከቱት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ጦርነቱን የመረጡ በመሆናቸው ምንም ውጤት አላስገኘም፡፡”

የአውሮፓ ህብረት ውሳኔ የወጣው የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ እየተቃረቡ መምጣታቸው በተነገረበት ወቅት ነው፡፡

ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች የአውሮፓ አገራት በተጨማሪ፣ በሞስኮ ላይ የተጣለው ይህ የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው፡፡

ሩሲያው ውስጥ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ባለ አንድ የባቡር ጣቢያ ላይ የሚጫኑ የጦር ተሽከርካሪዎች እኤአ የካቲት 23 2022 (ፎቶ ኤፒ)
ሩሲያው ውስጥ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ባለ አንድ የባቡር ጣቢያ ላይ የሚጫኑ የጦር ተሽከርካሪዎች እኤአ የካቲት 23 2022 (ፎቶ ኤፒ)

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ላይ ያለምንም በቂ ምክንያት ተገቢ ያልሆነ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽማለች ባሏት ሩሲያ ላይ ሌላኛውን ዙር ተጨማሪ ማዕቀብ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ በማድረግ መጀመራቸውን ተከትሎ የአየር ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ እግረኛ ወታደሮች ድንበሩን አቁርጠው ሲገቡ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ የአደጋ መስጫ ድምጾች የማስጠንቀቂያ ድምጽ ያሰሙ ነበር፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም ትናንት ሀሙስ ዜጎች ትጥቆቻቸውን እንዲያነሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባይደን፣ ከቡድን ሰባት አገር መሪዎች ጋር በሞስኮ ላይ እንዲጣል በጋራ የተቀናጀው አዲስ ማዕቀብ ውጤት ማሳየቱን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል

“በሩሲያ ገንዘብና ሩብል ላይ ያሳረፍነው ተጽ እኖ ከወዲሁ እያየነው ነው፡፡ ዛሬ ማለዳው ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝቅተኛ ዋጋ አሳይቷል፡፡ ዛሬ የሩሲያ የአክስዮን ገበያ በእጅጉ የወደቀ ሲሆን የሩሲያ መንግስት የብድር መጠን ጨምሮ ከ15 ከመቶ ከፍ ብሏል፡፡”

በቅርቡ የወጣው የማዕቀብ ሰነድ፣ በብዙዎቹ የሩሲያ ልሂቃን፣ በ13 የሩሲያ ድርጅቶች የእዳና የገቢ ማፍራት ፣ እንዲሁም ለሩሲያ ጦር ከዩናይትድ ስቴትስ የሚላከውን የቴክኖሎጂ ግብአቶች እና በሩሲያ ዋና ዋና የፋይናስ ተቋማት ላይ ገደብ የሚጥል ነው፡፡

ከውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ሃይዲ ክሬቦ ስለማዕቀቡ ይህን ብለዋል

“ሁለቱ ትላልቅ የመንግስት ባንኮች፣ ማለትም ሰበርባንክ እና ቪቲቢ፣ በሩሲያ የፋይንስ ስርዓት ውስጥ ወሳኞችና ትልቅ ድርሻ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ የአገሪቱን አብዛኛውን የዶላር ልውውጥ የሚያስተናግዱት የእነዚህ ሁለት ባንኮች በማዕቀቡ መካተት እጅግ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡”

ማዕቀቡ የክሬምሊን አጋር ከሆነቸውና በዩክሬን ላይ ጫና ለማሳደር ከሩሲያ ጦር ጋር ወታደራዊ ልምምድ ያካሄደችው ቤላሩስንም ይጨምራል፡፡

በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች እየተጣሉ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:22 0:00

ዩናትይድ ስቴትስና አጋሮችዋ ሞሶኮን “ስዊፍት” ከተባለውና በመላው ዓለም የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ባንኮችን ከሚያገናኘው የባንክ ሥርዐት ለማስወገድ ገና አልወሰኑም፡፡

በፕሬዚዳንት ፑቲንም የግል ንብረት ላይም ማዕቀብ ገና አልተጣለም፡፡ ይሁን እንጂ እነሱ አማራጮች አሁንም እንዳሉ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

ሮይተርስና ኢፖዝ በጋራ ባወጡት የህዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ ድምጽ መሠረት 69 ከመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ይደግፋሉ፡፡ 62 ከመቶ የሚሆኑት ግን ወደ ዩክሬን ወታደር መላክን አይደግፉም፡፡ ፕሬዚዳንት ባይደንም ይህን እንደማያደርጉ በተከታታይ ገልጸዋል፡፡

ቻትሃም ሀውስ ከተባለው ተቋም በሩሲያ ጉዳይ የተካኑት ኬር ጊልስ እንዲህ ይላሉ

“ምዕራባውያን አገሮች ከእውነታው ርቀው ዩክሬንን በቀጥተኛ ወታደራዊ ኃይል ለመከላከል እንደሚቻል የቱንም ያህል ቢያስቡ እንኳ፣ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ግን በይፋ መለፈፍ አይኖርባቸውም፡፡”

ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ሀሙስ የኔቶ አጋሮችዋን ለማገዝ 7ሺ የሚሆኑ ወታደሮችዋን ወደ ጀርመን ልካለች፡፡ ይህ በቅርቡ ወደ ፖላንድና ሩማኒያ ከላከችው በተጨማሪ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ100 በላይ የሚሆኑ የኔቶ የጦር አውሮፕላኖችና ከ150ሺ በላይ የሚሆኑ ወታደሮች በተጠነቀቅ እንዲጠባበቁ ታዘዋል፡፡

የኔቶ መሪዎች ቀጣዩ እምርጃቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመነጋገር ዛሬ ዓርብ በድረ ገጽ እንደሚሰበሰቡም ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG