የ’ሎርድ ሪዚስታንስ አርሚ’ (LRA) የቀድሞ የበታች አዛዥ የነበረው ቶማስ ክዎዬሎ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈጽሟል ሲል አንድ በኡጋንዳ የሚገኝ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል።
በሃገሪቱ የመጀመሪያው ነው በተባለው የጦር ወንጀል የፍርድ ሂደት፣ ቶማስ ክዎዬሎ 44 ክሶች ቀርበውበት በሁሉም ጥፋተኛ ተብሏል።
ቶማስ ክዎዬሎ ለሁለት አሥርት ዓመታት በሰሜን ኡጋንዳ በተካሄደው ደም አፋሳሽ አመጽ ወቅት ወንጀሉን ፈጸሟል በሚል ለዓመታት በእሥር ላይ ቆይቷል።
ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሰቆቃ፣ ጠለፋ እና የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሰፈራ ማውደም ጥፋተኛ ከተባሉበት ወንጀሎች ውስጥ እንደሆኑ ዳኛው ተናግረዋል።
ገና በ12 ዓመቱ በ’ሎርድ ሪዚስታንስ አርሚ’ (LRA) ተጠልፎ የተወሰደው ቶማስ ክዎዬሎ በተከሰሰባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ አለመሆኑን ተናግሯል።
የበታች አዛዥ እንደነበር የተነገረው ቶማስ ክዎዬሎ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት በእ.አ.አ 2009 የቀጠናው ሃገራት ኃይሎች የ’ሎርድ ሪዚስታንስ አርሚ’ አማጺያንን በሚያሳድዱበት ወቅት ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ ነበር የተያዘው።
በእ.አ.አ 2011 ለፍርድ ቢቀርብም፣ ለሌሎች ተዋጊዎች የተሰጠው ምህረት ለእርሱም ይገባዋል በሚል የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በነፃ አሰናብቶት ነበር። ከሳሽ አቃቤ ሕግ ይግባኝ በማለቱ መልሶ ለፍርድ ሊቀርብ በቅቷል።
በፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ላይ በተደረገው የአመፃ ጦርነት፣ ከመቶ ሺሕ በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ 60 ሺሕ የሚሆኑ አዳጊዎች ደግሞ ተጠልፈዋል።
መድረክ / ፎረም