በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩጋንዳ በደረሰ ፍንዳታ 74 ሰዎች ተገደሉ


አስር ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን መሞታቸው ተዘግቧል

ትናንት እሁድ ማታ የአለም ዋንጫ ፍጻሜን በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ በርካታ ሰዎች ተሰባስበው ሲመለከቱ ነበር ተከታታይ ፍንዳታዎች የኳስ አፍቃሪዎቹ የተሰበሰቡባቸውን ሁለት ስፍራዎች ያናወጡት።

አንደኛው የዩጋንዳ ራግቢ ክበብ ሲሆን፤ ሁለተኛው በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያን፣ የሌላ አገሮች ዜጎችና ዩጋንዳዊያን የተሰባሰቡበት የኢትዮጵያዊያን የገጠር ምግብ ቤት ነበር።

“የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ በማብቃት ላይ ሳለ ነው ፍንዳታው የተከሰተው…ወዲያው ሰው መጮህ ጀመረ፣ ከአካባቢው ለመራቅ በነጫጭ የፕላስቲክ ወንበሮች ላይ እየዘለለ ነበር የሚሄደው፣” ሲል ላለፉት ስድስት ወራት በካምፓላ የኖረውና ለጋዜጠኝነት ትምህርት ወደዚያው ያመራው ተስፋለም ወልደየስ ለቪኦኤ ተናግሯል።

በተመሳሳይ ሰአት በዩጋንዳ ራግቢ ክበብ የደረሱ ፍንዳታዎችም እንዲሁ በርካታዎችን አቁስለዋል። ዛሬ ማለዳ የዩጋንጋ ፖሊስ ኮሚሽነር በሰጡት መግለጫ የሟቾቹ ቁጥር 74 ሲደርስ ከሰባ የማያንሱ ደግሞ ቆስለዋል። መሟቾቹ መካከል ወደ አስር የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን እንደሚገኙበት ታቋል።

በተለያዩ ዜጎች የሚዘወተረው የኢትዮጵያ ምግብ ቤት የደረሰው ፍንዳታ አንድ-አሜሪካዊ መግደሉም ተዘግቧል።

“አንድ አሜሪካዊ ሞቷል። ጉዳት የደረሰባቸውን አሜሪካዊያን አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማጠያየቅ እየሞከርን ነው፣” ሲሉ በካምፓላ የዩናይትድ ስቴይትስ ኢምባሲ ቃል አቀባይ ጆዋን ሎካርድ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ መሪዎች መግለጫ አውጥተዋል። የዩናይትድ ስቴይትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ “አሳፋሪ የፈሪዎች ተግባር ሲሉት” የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን የዩጋንዳ መንግስት ወንጀለኞቹን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ቃል-አቀባይ በረከት ስም-ኦን በአልሸባብ የተሰነዘረ “የፈሪ ዱላ” ብለውታል።

የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አገራቸው በሞቃዲሹ ካላት ሀላፊነት አታፈገፍግም ብለዋል። ፕሬዝደንቱ ይህንን የተናገሩት አስቀድሞ የነበረውን ጥርጣሬ በመመርኮዝ ነው። ጉዳቱ እንደደረሰ- በአል-ቃይዳ የሚታገዘው የሶማሊያ የሽብርተኞች ቡድን አል-ሸባብ የአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃቱን በማቀነባበር በመጠርጠሩ ነው። ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙንት እንዳለው የሚነገረው የሶማሊያ አንጃ አል-ሸባብ ጥቃቱን መፈጸሙን ሰኞለት አምኗል።

“በካምፓላ የተከሰተው አገሪቱ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ስራ ላይ ከመሰማራቷ ጋር የተያያዘ ነው፣” ሲሉ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር ራምታኔ ላማምራ ዛሬ በአዲስ አበባ ተናግረዋል። ሚስተር ላማምራ ጥቃቱ የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ በአስቸኳይ ሊያሰፍር ያሰባቸውን የ2ሽህ ወታደሮችና አጠቃላይ የ8ሽህ ግብረ-ሀይል እቅድ አያስተጓጉለውም፤ እንዲያውም ከምን ጊዜውም በበለጠ ሁኔታ በሶማሊያ የሚኖረንን ስራ ያጠናክረዋል ብለዋል።

በካምፓላ ከደርግ አስተዳደር ጀምሮ በአሁኑ መንግስትም ጭምር በፖለቲካ ስደትና በንግድ የሚኖሩ በሽዎች የተቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ይገኛሉ።

XS
SM
MD
LG