በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አዲስ አበባ ላይ አርባ የአንድነት ሰዎች መታሠራቸውን ፓርቲው ገለፀ


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ

“የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ብሎ የሰየመውን መርኃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ያለው የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አርባ የሚሆኑ አባላቱ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ መታሠራቸውን ፓርቲው ለቪኦኤ አስታውቋል፡፡





please wait

No media source currently available

0:00 0:11:14 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

“የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ብሎ የሰየመውን መርኃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ያለው የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አርባ የሚሆኑ አባላቱ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ መታሠራቸውን ፓርቲው ለቪኦኤ አስታውቋል፡፡

የፓርቲው አባላት የታሠሩት ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው የሚለው ፀረ-ሽብር ሕጉ እንዲሠረዝ ለመጠየቅ የዜጎችን ፊርማ እያሰባሰበ ያለበትን ቅስቀሳ የያዙ በራሪ ወረቀቶችን እየበተኑ ሳሉ መሆኑን የፓርቲው አመራር አባላት ተናግረዋል፡፡

ወደ ስቱዲዮ እስከገባንበት ሰዓት ድረስ በየካ ክፍለ ከተማ 12፣ በአዲስ ከተማ 10፣ በጉለሌ 7፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ 11 ሰዎቻቸው የደንብ ልብስ በለበሱ ፖሊሶችና የደንብ ባልለበሱ ማንነታቸው የማይታወቅ ሰዎች ተይዘው መታሠራቸውን የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ዞን ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ግብረኃይል ፍላየርና ብሮሹር የማሰባሰብ እና የመበተን ኃላፊዋ ወ/ት ወይንሸት ስለሺ ገልፀዋል፡፡

የደንብ ልብስ ያልበሱት ሰዎች ማንነታቸውን እንኳ እንደማያሳውቁ የተናገሩት ወ/ት ወይንሸት አባሎቻቸውን ሲያስሩ የሽብር አድራጎት ታነሣሣላችሁ እንደሚሏቸው ገልፀዋል፡፡

ፓርቲው ይህንን ቀደም ሲልም በዕቅድ ይዞና የመንግሥቱን ጨምሮ በሃገር ውስጥና በዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን አሣውቆ እያከናወነ ያለውን መርኃግብሩን እንደማያቆም ያስታወቁት ወ/ት ወይንሽት ሰሞኑንም የፓርቲው ከፍተኛ የአመራር አካላት የሚሣተፉበት ተመሣሣይ ዘመቻ ለማድረግ ያቀዱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ሲሣይ ስለተባለው ሁኔታ እንደማያውቁና መረጃዎችን አሰባስበው መግለጫ እንደሚሰጡን ነግረውናል፡፡

ተጨማሪ ዝርዝር ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያገኛሉ፤ ያዳምጡት፡፡

/በድምፁ ውስጥ ከወ/ት ወይንሸት ድምፅ በስተጀርባ የሚሰማው ድምፅ በአካባቢው ከነበረ የእምነት ተቋም ይወጣ የነበረ መሆኑን እየገለፅን ለተፈጠረው የድምፅ መደረብ፤ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡/
XS
SM
MD
LG