በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስዊችብሌድ-600 “አንዣባቢው አጥፍቶ ጠፊ ሰዋልባ”


ስዊችብሌድ-600 “አንዣባቢው አጥፍቶ ጠፊ ሰዋልባ”
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:35 0:00

በዩክሬይን የጦር ሜዳዎች ላይ፣ የተሻለ ዐቅም ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መታየት የጀመረው፣ በሚያዝያ ወር መጨረሻ ነበር፡፡ ይህ “Switchblade -600” ተብሎ የሚጠራው “ሰዋልባ”(ድሮን)፣ ስዊችብሌድ- 300 ከሚባለው የቀድሞ ድሮን ተሻሽሎ የተሠራ ነው።

“Switchblade” ወይም “አንዣባቢው” ተብሎ የተሠየመው ዘመናዊ ድሮን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ዩክሬን ከተላኩት የውጊያ መሣሪያዎች አንዱ ነው።

በዩናይትስ ስቴትስ ካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኘው “ኤይሮ ቪሮንመንት” በተሰኘው ኩባንያ የተመረተው “ሰዋልባ”ው፣ ሁለት ዓይነት ምርቶች አሉት። ስዊችብሌድ-300 እና ስዊችብሌድ-600 ተብለው ይታወቃሉ። ስዊችብሌድ-600ው፣ “ካምዛከ” ተብሎም ይጠራል። ይህ “ሰዋልባ”፣ ከ2022 መጸው ወር አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፣ በዩክሬይን አየር ላይ እያነዣበበ የተሰጠውን ግዳጅ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከስዊችብሌድ-600 ቀድሞ የተሠራው ስዊችብሌድ-300፣ አነስተኛ እና አንድ ተዋጊ ወታደር ልክ እንደ ማሲኖዳው በጀርባው ተሸክሞት ከቦታ ቦታ ሊያንቀሳቅሰው የሚችለው መሣሪያ ነው፡፡

ጆን አልደን፣ የ “ሰዋልባው” ፕሮግራም ሥራ አኪያጅ ናቸው።

‹‹ሰዋልባው በራሱ 2ነጥብ5 ኪሎ ግራም ይመዝናል፡፡ መያዣ ቱቦውን ሲጨምር ደግሞ ወደ አምስት ኪሎ ግራ ይመዝናል። አንድ ወታደር፣ በጀርባው ከሚሸከመው ቦርሳው ጋራ ሦስት ሰዋልባዎችን በቀላሉ ተሸክሞ መጓዝ ይችላል፡፡ ለጉዞ የማዘጋጀቱ ሥራም፣ ከሁለት ደቂቃ በላይ አይወስድም፤ ቀላል እና ምቹም ነው፡፡”

ተሻሽሎ የተሠራው ስዊችብሌድ ዓይነት 600፣ በአንድ ሰዓት 185 ኪ.ሜ. መብረር ይችላል፡፡ ይህ በራሪ አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ፣ ወደተላከበት ዒላማ ሲደርስ፣ አየር ላይ በመቆም፣ ዒላማውን ፎቶ ግራፍ በማንሣት ወደ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ይልካል፡፡ በተላከው ፎቶ ላይ ጥናት ከተደረገ በኋላ፣ ዒላማውን እንዲደመስስ

ወይም እንዲመታ ትዕዛዝ ሲደርሰው፣ ወደ ዒላማው ተምዘግዝጎ በመወርወር ይላተማል፤ አጥፍቶ ይጠፋል፡፡

ስዊችብሌድ ዓይነት 600፣ ቀድሞ ከነበረው ስዊችብሌድ ዓይነት 300፣ በክብደት ከመብለጡም በላይ፣ ብዙ ሰዓት በአየር ላይ የመቆየት ብቃት አለው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን፣ በአየር ላይ እያንዣበበ በሚቆይበት ወቅት፣ የዒላማውን ሥሥ ብልት አንጥሮ የመለየት ችሎታ አለው፡፡

በአንድ ጊዜ ቦምብም አውሮፕላንም የኾነው ይህ መሣሪያ፣ የታንኮችን ሥሥ ብልት አነጣጥሮ በመምታት እና ከሥራ ውጭ በማድረግ ወይም በመደምሰስ ብቃቱ ይወደሳል፡፡ የታንኮችን ብረት፣ በቀላሉ መብሳት የሚችል ጉልበት አለው፡፡

ጆን አልደን ስለዚኽ ሰዋልባ አንዣባቢ ወይም በራሪ ቦምብ ብቃት እንዲህም ይላሉ፤

“ሊንቀሳቀስ ይችላል፤ ምናልባት ለመምታትም አስቸጋሪ ሊኾን ይችላል፡፡ በዒላማው ዙሪያ ስለሚያንዣብብ፣ ኦፕሬተሩ፥ ዒላማው እይታ ውስጥ እስኪገባለት ድረስ አየር ላይ እያንዣበበ ጠብቆ ሰለባውን ማስወገድ ይችላል፡፡”

“ሰዋልባው”ን ያመረተው ኩባንያ እንዳለው፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ 1000 የሚኾኑ አጥፍቶ ጠፊ በራሪ ቦምቦችን ወደ ዩክሬይን ልካለች፡፡

ዋህድ ናዋቢ፣ ይህን ሰዋልባ በራሪ የሚያመርተው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ይህ ሰዋልባ፣ በአሁን ሰዓት፣ በግዙፍ የጦር ተቋማት ውስጥ፣ በዐውደ ውጊያ እያገለገሉ ካሉት ጋራ ሲነጻጸር፥ ርካሽ፣ ቀላል፣ ተነቃናቂ እና የበለጠ ቀልጣፋ እንደኾነ፣ ሥራ አስኪያጁ ዋህድ ናዋቢ ይናገራሉ፡፡

“በጣም አነስተኛ ወታደራዊ ኃይል ያላት ዩክሬን፣ በውጊያ ችሎታዋ እጅግ አስገራሚ ናት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፥ ሰዎቿ መንፈሰ ጠንካሮች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፥ ተልዕኮአቸውን ለማሳካት እንዲችሉ፣ የጦር መሣሪያዎች እና የጦርነት ቁሳቁሶች፣ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ እኛ የምንሠራቸው ሰዋልባዎች እና ጥይቶች፣ ለማመን የሚከብዱ ውጤታማዎች እና ለውጥ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡”

በመጨረሻም፣ ይህ “የአንዣባቢው ሰዋልባ” በራሪ ቴክኖሎጂ፣ የመጪዎቹን ወራት የዘርፉን ትልም እንደሚወስን ናዋቢ ተናግረዋል፡፡

/ክርስቲና ሼቪሼንኮ፣ የዚኽን ድሮን ማምረቻ በመጎብኘት ያጠናቀረችውን ዘገባ በፈቃዱ ሞረዳ፣ ወደ ዐማርኛ መልሶታል/

XS
SM
MD
LG