ዩናይትድ ስቴትስ በሞቃዲሾ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቋን ተከትሎ ቢያንስ ሁለት ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ማክሰኞ ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ ሊያደርጉት የነበረውን በረራ ሰርዘዋል።
በረራቸውን የሰረዙት የቱርክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች ሲሆኑ፣ ሞቃዲሾ በሚገኘው ኤደን አዲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት ከሚሰጡ ዋና የማጓጓዣ ተቋማት መሃል ይጠቀሳሉ። አየር መንገዶቹ በረራቸውን የሰረዙት ከደህንነት ማስጠንቀቂያው ጋራ ተያይዞ መሆኑን እንደሚያምኑ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየት ለመስጠት ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት የቱርክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞችም በረራዎቹ መሰረዛቸውን ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል።
የቱርክ አየር መንገድ ሠራተኛ በረራው የተሰረዘው "ከሥራ ሂደት ጋራ በተያያዘ ምክንያት" መሆኑን የገለፀ ሲሆን፣ በበረራ መርሐ ግብሩ ላይ ዘግይቶ የሚደረግ ለውጥ ከሌለ በስተቀር አየር መንገዱ ነገ ሥራውን እንደሚቀጥል አመልክቷል።
በሞቃዲሾ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ በበኩሉ አየር መንገዱ የዛሬውን በረራ የሰረዘው "በቂ መንገደኞች ባለመኖራቸው" መሆኑን ለአሜሪካ ድምፅ ሶማሌ አገልግሎት ተናግሯል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የነገውንም በረራ "በሥራ ሂደት ችግር" ምክንያት መሰረዙንም ገልጿል።
ናይሮቢ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በሶማሊያ ዋና ከተማ፣ ሞቃዲሾ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ሊፈፀሙ ስለታቀዱ ጥቃቶች መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል። ለጥቃቱ ዒላማ ተደርገው ከተለዩ ቦታዎች ውስጥም አንዱ በከተማው የሚገኘው ኤደን አዲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አንዱ መሆኑንም ገልጿል።
የአየር ማረፊያው በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ቡድን እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የበርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ኤምባሲዎች መቀመጫ ሆኖም ያገለግላል።
የኤምባሲው ማስጠንቀቂያ አክሎ "የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች፣ ማክሰኞ ሚያዚያ 1፣ 2016 ዓ.ም የሚኖራቸው ሁሉም እንቅስቃሴዎች ተሰርዘዋል" ብሏል።
የሶማሊያ መንግስት ባለሥልጣናት ግን፣ አውሮፕላን ማረፊያው አሁንም ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ በረራ ክፍት መሆናቸውን እየገለፁ ሲሆን፣ የትራንስፖርትና ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር "አየር መንገዱ ክፍት ነው" ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ሶማሌ ቋንቋ አገልግሎት ተናግረዋል።
"እንደ ኡጋንዳ ያሉ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች መተዋል። ሰዎችም ወደ ናይሮቢ ተጉዘዋል። ወደ ክልሎች የሚደረጉ የሀገር ውስጥ በረራዎችም ክፍት ናቸው" ብለዋል።
የአየር መንገዶቹ በረራቸውን መሰረዝ የሶማሊያ መንግስት ውሳኔ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ አየር መንገዶቹ በረራቸውን መሰረዛቸውን አስመልክቶ ለሶማሊያ መንግስት ምንም አይነት መረጃ አለመስጠታቸውንም ተናግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ የጸጥታ ስጋቱ ከየት እንደመጣ ባትገልጽም የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን በሶማሊያ መንግሥት፣ በአፍሪካ ኅብረት ኃይሎችና በሶማሊያ በሚደግፉ አገሮች ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ቆይቷል።
መድረክ / ፎረም