በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ ፌደራል ክሥ ሊመሠረትባቸው ነው


የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ከወጡ በኋላ የመንግሥት ምሥጢር የያዙ ሰነዶችን ባልተገባ ሁኔታ በግል መኖሪያቸው በማቆየት ዛሬ ይመሠርትባቸዋል የተባለውን ክሥ ለመስማት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

የክሡ ሂደት ፍሎሪዳ ግዛቷ ማያሚ ከተማ በሚገኘው ፌደራል ፍርድ ቤት ውስጥ በዋሽንግተን ዲሲ አቆጣጠር ዛሬ ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት (አዲስ አበባ ላይ ማታ አራት ሰዓት፤ ለንደን ላይ ከምሽቱ 1 ሰዓት ወይም 1900 ጂኤምቲ) ላይ ይጀመራል ተብሏል።

ፌደራል ባለሥልጣናት በፍርድ ቤቱ ዙሪያ ያለውን የፀጥታና ደኅንነት ጥበቃ ያጠናከሩ ሲሆን እስከ ሃምሣ ሺህ የሚደርሱ ተቃዋሚዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን የከተማዪቱ ባለሥልጣናንት ገልፀዋል።

ሆኖም እስከ ዛሬ (ማክሰኞ) ረፋድ ምንም ዓይነት የሁከት አጋጣሚ ወይም አዝማሚያ አልተዘገበም።

ትረምፕ ፍርድ ቤት የሚቀርቡት የስለላ ህጉን በመጣስ 'የሃገሪቱን የመከላከያ ሚሥጥራዊ ሰነዶችን ሆን ብለው መውሰዳቸውን' የሚያመለክቱ 31 የክሥ አንቀፆችን ጨምሮ በ37 የወንጀል ክሦች እንዲጠየቁ ማያሚ የሚገኙ የፌደራል ዳኞች ስብስብ ውሳኔ ካሳለፈ ከአምስት ቀናት በኋላ ነው።

እያንዳንዱ ክሥ እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ እሥራት እንደሚያስቀጣ ህግ አዋቆች እየተናገሩ ነው። በቀድሞም ይሁን በተቀማጭ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ላይ ፌደራል ዶሴ ሲከፈት ትረምፕ የመጀመሪያ ሲሆኑ የዛሬው በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዳኛ ፊት የሚቀርቡበት ሁለተኛ ክሥ መሆኑ ነው።

XS
SM
MD
LG