ዋሺንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ሱዳንና እስራኤል ግንኙነታቸውን ማዳሳቸውን ዛሬ አስታውቀዋል። ሌሎች ሀገሮችም ምናልባትም በጥቂት ወራት ውስጥ የሱዳንን ፈልግ ይከተላሉ ብለዋል።
ስምምነቱ ሳውዲ አረብያን፣ ፍሊስጤምንና ምናልባትም ኢራንን ሊያቅፉ እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ትረምፕ ስለስምምነቱ የገለጹት በዋይት ኃውስ ቤተ መንግሥት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁና ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ጊዜ ነው።
ትረምፕ በስልክ ንግግራቸው ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሱዳኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክን ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብደላ ሐምዶክም ኢትዮጵያ ከዋሺንግተኑ ውይይት ራሷን በማግለሏ ግብጽ ደስተኛ እንዳልሆነች ጠቅሰው ግድቡ ለሦስቱም ሃገራት ጠቃሚ በመሆኑ በሦስትዮሽ ውይይት መፍትሄ እንደሚገኝ ተስፋ አሰምተዋል።
ፕሬዚዳንት ትረምፕ ግን የግድቡ ግንባታ ግብጽን እንደሚጎዳ ጠቅሰው “ግብጽ ግድቡን ማፈንዳት አለባት” ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አስተዳደራቸው ኢትዮጵያን የእርዳታ ገንዘብ እንደከለከለ አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ በውይይቱ መሳተፍ ካልቀጠለች ገንዘቡን አታይም ሲሉ ዝተዋል።