ዋሺንግተን ዲሲ —
ሦርያ ፈጽማለች ተብሎ ለተጠረጠረው የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጥቃት ምን እርምጃ እንደሚወስዱ አሰተዳደራቸው እያጠና መሆኑን የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አስታወቁ።
ትናንት ማታ ከከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ሲናገሩ፣ “ኃይል የተቀላቀለበት አፀፋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ማለታቸው ተሰምቷል።
ባለፈው ቅዳሜ ለደረሰው ኬሚካዊ ጦር መሣሪያ ጥቃት የዩናይትድ ስቴትስ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ዋና ዋናዎቹን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ በወታደራዊ ረገድ እንኳ፣ በግልፅ ባይናገሩትም፣ ሦስት አማራጮች እንዳሉ ነው የጠቆሙት።
ትረምፕ ባለፈው ዓመት በአንድ የሦርያ አየር ማረፊያ ላይ የኬሚካል ጥቃት እንዲካሄድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ወታደራዊ እርምጃዎችን አስቀድሞ ይፋ የሚያደርግ ደካማ ስትራተጂ ነበራቸው ሲሉ ትረምፕ ይነቅፋሉ።
ሦርያ፣ አገሯ ላይ ውዝግብ ከተቀሰቀሰበት እአአ ከ2011 ጀምሮ፣ ያለፈውን የቅዳሜ ጥቃት ጨምሮ፣ አንዳችም ኬሚካል ጦር መሣሪያ እንዳልተጠቀመች ነው የምታስተባብለው፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ