በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ለመነጋገር ትናንትና ዛሬ /ዕሁድ እና ሰኞ መስከረም 23 እና 24/ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የቴክኒክ ምክክር ስብሰባ ለጥቅምት አጋማሽ አካባቢ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡
የስብሰባውን መተላለፍ የገለፁት የግብፅ የውኃና የመስኖ ሚኒስትር ሆሳም ሞጋዚ ሲሆኑ ምክንያቱ ኢትዮጵያና ግብፅ ባሉባቸው የልዩ ምክንያቶች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አጥናፌ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ስብሰባው የተላለፈው በዚህ ወር ውስጥ በተመሣሣይ ጉዳዮች በርካታ አካባቢያዊ ስብሰባዎች ስለሚካሄዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አንዱ ስብሰባ ኢንተቤ ላይ የሚካሄድ የአሥሩ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ አባል ሃገሮች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ሲሆን ሌሎቹ ኪጋሊና አዲስ አበባ ላይ የሚካሄዱት የተፋሰሱ የደቡብና የምሥራቅ ሃገሮች የቴክኒክ ፅ/ቤቶች ስብሰባዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚፈስሱት ጅረቶች 92 ከመቶው ወሰን ተሻጋሪ ሲሆኑ የውኃ አጠቃቀም ፕሮቶኮል ወይም መግባቢያ ላይ ለመደራደር አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች የጋራ ትብብር ባለሥልጣን ኢጋድ ስብሰባም እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ስብሰባው እንዲተላለፍ የተደረገው ሃገሪቱ አዲሱን መንግሥቷን የምትመሠርተው ነገ ማክሰኞ፤ መስከረም 25 በመሆኑ ‘የካቢኔ ለውጥ ሊኖር ይችላል’ በሚል እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ተሾመ አጥናፌ ስብሰባው የቴክኒክ መሆኑንና ሚኒስትሮች እንዲገኙ እንደማይጠበቅ ገልፀዋል፡፡
የስብሰባው አጀንዳ ገና በዝርዝር እንደማይታወቅ አቶ ተሾመ በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በተካሄደው የአማካሪ ድርጅቶች መረጣ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ፈረንሣዊው ቢአርኤል በዋና ተቋራጭነት፣ ሰባ ከመቶ የሚሆነውን፤ በግብፅ ቀርቦ የነበረው የሆላንዱ ዴልታሬስ በበታች ተቋራጭነት ሰላሣ ከመቶውን ሥራ ሊሸፍኑና ዴልታሬስ በዋናው ተቋራጭ ክትትል ሊሠራ ተወስኖ እንደነበር ይታወሣል፡፡
ቆየት ብሎ ዴልታሬስ ከተቋራጭነት ሥራው እራሱን ማውጣቱን አሳውቋል፡፡ ሥራውን በዋና ተቋራጭነት እንዲያከናውን የተመረጠውን የፈረንሣዩን ቢአርኤልን ደግሞ ግብፃዊያኑ እምብዛም እንደማይደግፉት፣ ወይም በጥርጣሬ እንደሚያዩትና በኩባንያው ደስተኛ እንዳልሆኑም ይሰማል፡፡
የኅዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘው ዕቅድ መሠረት እየተካሄደ መሆኑን እስከአሁንም 47 ከመቶው መጠናቀቁንና ይጠናቀቃል ተብሎ በታቀደለት ጊዜም ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክተሩ አቶ ተሾመ አጥናፌ በዚሁ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ገልፀዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡