በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
ታይም መፅሄት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በዓመቱ የዓለም 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ አካተተ

ታይም መፅሄት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በዓመቱ የዓለም 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ አካተተ


ፎቶ ፋይል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ፎቶ ፋይል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

- መፅሄቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የገለፀበትን መንገድ ቃል አቀባያቸው ነቅፈዋል

“ታይም [TIME]” መፅሄት የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን እአአ በ2022 ዓ.ም. የዓለም 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ አካትቷቸዋል።

በዝርዝሩ እንዲካተቱ የተደረጉት በእርሳቸው አመራር በሃገሪቱ ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት በመካሄዱ እንዲሁም ጦራቸው በጅምላ ግድያ፣ በፆታ ጥቃትና ዘር በማፅዳት በመከሰሱ መሆኑን ጠቅሷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የፕሬስ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ይህን በመቃወም ለታይም መጽሔት በላኩትና ለአሜሪካ ድምፅ በደረሰው ኢሜል መፅሔቱ “ሆን ብሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም በሚያጎድፍ መንገድ አንድ መቶ ተፅዕኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ ከትቷቸዋል” ብለዋል።

መፅሄቱ ባወጣው ዝርዝር “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀገራቸው ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የነበራትን የዓመታት ግጭት በመፍታታቸው እአአ በ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሲሆኑ በቀጣናው የተሻለ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ተስፋ ጭሮ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የርስ በርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስም መነሻ ዘር ዘርቷል” ብሏል።

“19 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት በሌላ አገላለፅ በትግራይ ተወላጆች ላይ ጭካኔ የተፈፀመበት ድርጊት ሊባል ይችላል” ሲል መፅሄቱ አስፍሯል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ቢልለኔ ስዩም “ይህ የመፅሄቱ አሳዛኝ የሆነ አቋም በአማራና በትግራይ ክልሎች ‘አሸባሪ’ ሲሉ በጠሩት “ቡድን ለተፈፀመውና ለተቀጠፈው ህይወት በአፈ ቀላጤነት የተሰለፈበትን ሁኔታ ያሳያል” ብለዋል።

ታይም በዘገባው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ጠቁሞ ይቀጥልና “ባለፈው መጋቢት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ለማድረስ እንዲቻል ተኩስ እንዲቆም ቢያውጁም አምና ሰኔ ውስጥ እንዳደረጉት፡ በሰብዓዊነት ምክንያት ተኩስ ማቆሙ ሥልታዊ ይመስላል፤ ለትግራይ የደረሰው ዕርዳታ ጥቂት ነው” ብሏል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራይ አማፂያንን “አረም” ብለው መጥራታቸው የጥላቻ ንግግር ከፍ ማለቱን ያሳያል” ብሏል አክሎ።

ቢልለኔ ስዩም “መፅሄቱ ሆን ብሎ ህወሓት ጦርነቱን መጀመሩን ማመኑን የሚመለከቱና ሌሎችንም ባለፈው ዓመት የወጡ ሪፖርቶችን ሳይጠቅስ ማለፉን” በኢሜላቸው ጠቅሰዋል። እንደማሳያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባወጣው ሪፖርት ላይ “ኖቬምበር 3/2020 ዓ.ም. የትግራይ ልዩ ኃይልና ተባባሪው ሚሊሺያ የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊትን የሰሜን ዕዝ ማጥቃታችውን፣ የጦር ሠፈሩንም መቆጣጠራቸውን፤ ኖቬምበር 4/2020 ዓ.ም. ፌዴራል መንግሥቱ በህወሓት ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማድረጉን” የሚጠቁመውን ሪፖርት ጠቅሰዋል።

ቃል አቀባይዋ አክለውም መጽሄቱ በምርምራ የተገኙ እውነታዎችን ትቶ የራሱን ትርክት ለምን መረጠ ሲሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

መፅሄቱ በተጨማሪም የኖቤል ኮሚቴው ባለፈው ጥር ባልተለመደ ሁኔታ “ጦርነቱን ለማስቆምና ሰላምን ለመቀጠል የተለየ ኃላፊነት አለባችው” ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መንቀፉን አስታውሷል።

ፎቶ ፋይል፦ ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካዊቷ የሰው ሠራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንቴሊጀንስ) ባለሞያ ትምኒት ገብሩ
ፎቶ ፋይል፦ ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካዊቷ የሰው ሠራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንቴሊጀንስ) ባለሞያ ትምኒት ገብሩ

ታይም መፅሔት በተጨማሪም ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካዊቷ የሰው ሠራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንቴሊጀንስ) ባለሞያ ትምኒት ገብሩን ሲያካትት ትሠራበት የነበረው ጉግል "ዘረኛ አሠራር ይከተላል" በማለቷ ከቴክኖሎጂ ኩባንያው ሥራዋ መባረሯን ጠቅሷል።

ትምኒት በጉግል ቆይታዋ የሰው ሠራሽ ልህቀት ቡድንን ከሚመሩ ዋና ጥቁር ሴቶች አንዷ እንደነበረችና ቴክኖሎጂውን ለማሻሻል ትሠራ እንደነበር ጠቅሷል።

ይህንኑ ተግባሯን የሚያሳይ "በጉግል የሰው ሠራሽ ልህቀት ቴክኖሎጂ ዘረኛ አሠራር ያለውና የአካባቢ ጥበቃን የሚጎዳ መሆኑን" የሚያሳይ የጥናት ፅሁፍ ከባልደረቦቿ ጋር በትብብር በመፃፋቸው መባርራቸውን አስታውሷል።

ትምኒት በመስኩ ካሉ መሪ ተመራማሪዎች አንዷ ስትሆን የሰው ሠራሽ ልህቀት ቴክኖሎጂ ውስንነት እንዳለበትና ለምሳሌም የፊት መለያ ፕሮግራሞች (ፌሽያል ሬከግኒሽን ሾፍትዌር) ጥቁር ሴቶችን እንደማይለይ፣ በተጨማሪም በቴክኖሎጂው ዘርፍ የዘር መድልዎና ማግለል መኖሩን ዓለም እንዲረዳ ማስቻሏን ታይም መፅሄት ጨምሮ ገልጿል።

XS
SM
MD
LG