በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮች ሽረ እንዳስላሴ ላይ መፍሰሳቸው ተገለጸ


ሽረ እንደስላሴ ከገቡ ተፈናቃዮች መካከል
ሽረ እንደስላሴ ከገቡ ተፈናቃዮች መካከል

ሽረ እንዳስላሴ ከተማ ውስጥ ከ345,000 በላይ ተፈናቃዮች ትምህርት ቤቶችና የዛፍ ስር ሳይቀር ተጠልለው እንደሚገኙ ቪኦኤ ያነጋገራቸው ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከማይ ካድራና ከሌሎችም የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ንብረታቸው ተዘርፎ የተባረሩ እንዳሉና አሁንም እየተባረሩ መሆናቸውን አንዲሁም በኤርትራ ወታደሮች በወል የተደፈሩ ሴቶች እንዳሉ ተፈናቃዮቹ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የ65 ዓመት አዛውንቱ የስምንት ልጆች አባት አቶ ብርሃነ ንርኤ፣ የአሥር ሰው ቤተሰብ አባወራ መሆናቸውን ይናገራሉ። አቶ ብርሃነ እንደሚሉት “ከምዕራብ ትግራይ ሁመራ ከተማ አጠገብ ከሚገኘው መኖሪያቸው ‘ተባረው’፣ ሽረ እንዳስላሴ ከተማ ከገቡ ሳምንት ሆኗቸዋል።

“እኔ ገበሬ ነኝ። የምኖረው ነው። ግን ንብረቴንና የነበሩኝን እንስሶዎች ከዘረፉኝ በኋላ ጠብቄ ሁሉም ሰው ከወጣ በኋላ አይሆንልኝም፤ በረሃብ ብሞት ይሻለኛል ብየ ነው የመጣሁት። ወልቃይቶችና ሚሊሽያ ተብለው ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ሆነው ወደ አካባቢው የመጡት ናቸው ተባብረው አገሩን የዘረፉት። ወደ ሃያ የሚሆኑ በጎች ነበሩኝ። እህልም ነበረኝ። ሰሊጥና ሌላውን ከወረሩት በኋላ በጎቼን ሸጨ እዚሁ ቤቴ እሞታለሁ ብየ ነበር። በጎቹን ሲወስዱብኝ ግን ከዚህ በኋላ ወደ ህይወቴ ይመጣሉ ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነው የወጣሁት።”ብለዋል አቶ ብርሃነ ንረኤ።

አቶ ብርሃነ ንርኤ ከርሳቸው ቀድመው ሽረ እንዳስላሴ ከተማ የገቡት፣ በየትምህርት ቤቱና አውላላ ሜዳ ላይ እንደሚገኙና ከመመዝገብ ውጪ እስካሁን እህል ሲሰጥ አለማየታቸውን፤ ሰዉ ጭንቀትና ችግር ላይ እንደሚገኝ፤ እርሳቸውም እዚያ ከደረሱ ጀምሮ፣ ከአንዳንድ ወዳጆቻቸው ከሚያገኙት እርዳታ በስተቀር፣ከመንግሥት ምንም አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ከሁመራ ወጥተው ሲጓዙ በየመንገዱ የወዳደቀ አስከሬን ማየታቸውንና እርሳቸው የሚያውቋቸው ገበሬዎች፣ ገብረመድህን የሚባሉ ከነልጁጃቸው ባል፣ ከብቶቻቸውን ይዘው ሲሸሹ የመከላከያ ወታደሮች እንደገደሏቸው ይናገራሉ አቶ ብርሃነ።

“ህዝቡ አይዞህ ባይ የለውም፤ ከእንዳስላሰ ህዝብ እየተዋጣ ከሚሰጠው በስተቀር፣የሚበላው የሚጠጣውና የሚተኛበት የለውም። የሚመጣው እርዳታ ለህዝቡ እየተሰጠ አይደለም፤ የት እንደሚገባም አይታወቅም” ብለዋል።

ሰዉ አራት ወር ሙሉ ሽሽትና ጉዞ ላይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ብርሃኔ ቁጥሩን ማወቅ እንደማይቻል ገልፀዋል።

የልጆች እናት መሆኗን የገለፀችው ሰናይት ንጉሤ ታሕሳስ 12 / 2013 ዓ.ም. ከምትኖርበት ከማይ ካድራ በአማራ ታጣቂዎች እንደተባረረች ትናገራለች። “ይህ አገራችሁ አይደለም። የኛ መሬት፣ የኛ ቦታ ነው። እዚህ ትግራዋይ የሚሠራበት ቦታ አይደለም። ስደተኞች ናችሁ ይሉናል” ብላለች።

ባለቤትዋ ማይ ካድራ ውስጥ በተፈጠረው ሁኔታ፣ ይሙቲ ይኑሩ እንደማታውቅ፣ ልጆችዋን ይዘ ሸሽታ እንደወጡ ገልጻ“ደርሶብኛል” ስለምትለው በደል ስታስረዳ፣

“ወሲባዊና በእሳት የመለብለብ ጥቃት ተፈፅሞብኛል። የፈፀመው የሻቢያ ሰራዊት ሲሆን ጥቃቱ የተፈፀመብኝ ታህሳስ 14 / 2013 ዓ.ም. ነው። ትግራዋይ የሆንን በመኪና ጭነው ተከዜን አሻገሩን። ተከዜን ተሻግረን በእግራችን ተጉዘን ፀልሜ እንደደረስን ሻቢያ ተቀብሎ ፆታዊ ጥቃት ፈፀመብን። ከኔ ጋር አራት ልጆቼ ነበሩ። የስድስት ወር ህፃን ጀርባዬ ላይ ነበረች።ከቤቱ ጓሮ አስተኝተዋት እያለቀሰች አምስት ወታደሮች በተከታታይ እየተፈራረቁ ደፈሩኝ። ለሦስት ቀናት እዚያው አቆይተው የክላሽንኮቭ ዘንግ ብረት አጋይቶ ማህፀኔን ለበለበኝ።” ብላለች።

የወልቃይትና የአማራ ታጣቂዎች 93 የትግራይ ተወላጆችን በሲኖ ትራክ መኪና ጭነው፣ ተከዘን አሻግረው እንደጣሏቸው ሰናይት ገልጸዋል። ሁለት ሴቶች አንድ ቤት ውስጥ እንደተደፈሩና ሦስተኛዋ ግን ‘ኤች አይ ቪ አለብኝ’ በማለቷ እንደለቀቋት ጠቁማለች። ኤም ኤስ ኤፍ የሚባል ድርጅት ወደ ቀይ መስቀል ወስዶ ህክምና እንደተደረገላች ሰናይት ተናግራለች።

“አሁንም ግን ሽንቴን መቆጣጠር አልችልም። ውኃ አልጠጣም። በዛ ላይ የምኖረው በስደተኞች ሰፈር ነው። ሰዎች ከኪሳቸው ነው የሚያግዙኝ። ከዚያ ውጭ ልጆችን ይዤ ያገኘሁት ነገር የለም። ‘እርዳታ ይመጣል ጠብቁ’ ይባላል የት እንደሚገባ አይታወቅም። እንደኔ የሚያለቅሱ ብዙ አሉ።” ትላለች ሰናይት።

“ማህፀኔ ላይ ደርሶብኛል” በምትለውት ጉዳት ምክንያት መቀመጥ እንደማትችልና እንቅልፍ እንደሌላት ጊዜዋን የምታሳልፈው በምቆምና በመንበርከክ እንደሆነ ገልጻለች። “ምንም የሌላቸው በየትምህርት ቤቱና በየሥርቻው ተጥለው ያሉ ህፃናት የያዙ፤ በየጥጋ ጥጉ የሚወልዱ እናቶች አሉ። ዛሬም ሜዳ ላይ የወለዱ እናቶች አሉ። በጣም የተጨንቀ ሰው ነው የምታየው። ትግራዋይ በጣም ያሳዝናል” ብለዋል። እስካሁን ድረስ ከምንጣፍ ሌላ ያገኘችው እርዳታ እንደሌለ ገልጻለች። “መንግሥትና የዓለም ማኅበረሰብ ትኩረት ሰጥተው እንዲያግዙን እንጠይቃለን'' ብላለች።

ሰላሣ ዓመቷ እንደሆነና ሽረ እንዳስላሴ እንደምትገኝ የምትናግረው ሳራ ኪዳነማሪያም ደግሞ፣ ትኖርበት የነበረችው ሁመራ ከተማ በከብድ

መሳርያ ስትደበደብ፣ ሁለት መንታ ህፃናትን ጨምሮ፣ ሦስት ልጆቿን ይዛ መሸሿን፣ ከሦስት ቀናት የእግር ጉዞ በኋላ፣ ሽረ እንዳስለሰ እንደደረሰች፣ ከባለቤቷ ጋር መለያየቷንና ሱዳን ሃምዳይት የስደተኞች መጠለያ መግባቱን፣ከሁለት ወር በኋላ ማወቋን፣ አሁን በስልክ እንደሚገናኙ ትገልፃለች።

የሽረ እንዳስላሴ ነዋሪዎች ተፈናቃዮችን ለማገዝ ያደረጉት ርብርብ በጣም እንዳስደሰታትና እንደኮራች፤ ከተማው ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ሁኔታ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ትናገራለች።

ህፃናት ይዘው የሚበላ የሌላቸው እናቶች የባህር ዛፍ ቅጠል ላይ እንደሚተኙና እርሷም አንዳንዴ ለምና ከምታገኘው፣ ለአራሶች እንደምታካፍል ትገልፃለች ሳራ።

ሽረ እንዳስላሰ ከገባች በኋላ፣ የኤርትራ ወታደሮችና የፌደራል ኃይሎች ከተማዪቱን ለመያዝ ከባድ መሳሪያ ሲተኩሱ፣ ወደ እንዳባጉና ከዛም ወደ ደብረ አባይ ሸሽተው፣ በከባድ መሳሪያ ፍንጣሪ ጡቷ ላይ እንደቆሰለች የምትናገረው ሳራ፣ደብረ አባይ ላይ እንደሷ ከሁመራ የሸሹ በስም የምታውቃቸውን ሁለት ሰዎችና ሌሎች የማታውቃቸውን ሦስት ሰዎች የኤርትራ ወታደሮችና የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ከቤት ጎትተው አውጥተው ጁንታ እያሉ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደሏቸው ገልፃለች።

ወደ ሽረ እንዳስላሴ ከመጣች አምስተኛ ወርዋ እንድሆነና ጥቂት የእህል እርዳታ እያገኘች መሆኗን ተናግራለች።

ተፈናቅለው እንዳስላሴ ከተማ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች፣ በመቶ ሺሆች እንደሚቆጠሩ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዶ/ር ቴድሮስ አረጋይ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

“ሁኔታው እንደተፈጠረ ከምዕራብ ትግራይና ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞኖች ወደ ሽረ እንዳስላሴ ከተማ ብዙ ተፈናቃዮች ሲመጡ ቆይተዋል። ከምዕራብ ትግራይ ዞን 200,000 አካባቢ የሚሆን ሰው፣ ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ደግሞ ንብረታቸውና ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው ወደ 145,000 አካባቢ የሚሆኑ በአጠቃላይ ከ345,000 በላይ ተፈናቃዮች ሽረ እንዳስላሴ ከተማ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። 14 የሚሆኑ የመጠለያ ማዕከሎች አሉን።” ብለዋል።

ሰዎቹ የተፍናቀሉት ከተለያዩ የምዕራብ ትግራይ ከተሞች እንደሆነና፣ የሚያባርሯቸው ‘የተለያዩ የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው” እንደሚገልፁላቸው፣የዞኑ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዶ/ር ቴድሮስ ጠቁመዋል።

“በመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሦስት ወራት የሚመጡት የተፈናቃዮች ጥቂት ነበሩ። ሦስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ብቻ ነበር የተጠለሉት። ባለፉት ሁለት ሣምንት ውስጥ ግን ከ159,000 ባላይ ሰው ባንድ ጊዜ ተፈናቅሎ በ11 ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለዋል። ከምዕራብ ትግራይ ከቦታችን ልቀቁልን መባላቸውን፤ የመንግሥት ታጣቂዎች አይመስሉኝም፤ ግን ግለሰቦችና የታጠቁ ኃይሎች እንዳባረሯቸው ነው ተፈናቃዮቹ የሚነግሩን። አሁን እያናገርኩህ ባለበት ሰዓት እንኳ ከተለያዩ የምዕራብ ከተሞች እየገቡ ነው።” በማለት ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት በዞንና በክልል ደረጃ የ“እንነጋገር” መነሻ ሃሳቦችን፣ ወደ አጎራባች ዞኖችና ወደ ክልል ደብዳቤ ልከው፣ እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ፣ ዶክተር ቴድሮስ ተናግረዋል።

ከመንግስትና ከተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች፣ ብዙ እርዳታ እየደረሰ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ ከሰዉ ብዛትና በየቀኑ ከሚጎርፈው ተፈናቃይ ቁጥር አንፃር፣የሚላከው እርዳታ በቂ እንዳልሆነ ዶክተር ቴድሮስ አመልክተዋል።

የሽረ እንዳስላሴ ጎልቶ በመታየቱ እንጂ፣ በሸራሮ ከተማ ከባድሜና ከአካባቢው የተፈናቀሉ ከ80,000 በላይ ተፈናቃዮች፤ ከፀለምትና ከአካባቢው፣ ከእንዳባጉናና ሌሎችም አካባቢዎች የተፈናቀሉ፣ ብዛት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን አስተዳዳሪው ጠቁመው በ13ቱም ወረዳዎች እርዳታውን ‘'ለማቃመስ’’ መሞከራቸውን ገልፀዋል። ሽረ እንዳስለሴ ከሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ለአንድ መቶ ሰላሳ አንድ ሺ ተፈናቃዮች ለሁለት ወር የሚሆን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ እርዳታ ቢያከፋፍሉም፣ የሚፈለገውን ያህል አድርሰናል ብለው እንደማያምኑ፣ ጊዜያዊ አስተዳዳሪው አመልክተዋል።

ተፈናቃዮቹን ከተጨናነቁት መጠለያዎች ለማውጣት፣ ትላልቅ የመጠለያ ድንኳኖችን ለመትከል እየሠሩ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ዘላቂው መፍትኄ ግን ተፈናቃዮቹን ወደመጡበት መኖሪያቸው መመለስ እንደሆነ አሳስበዋል። መፍትሄው ግን በእርሳቸው እጅ አለመሆኑንና በፌደራል መንግሥቱ ሊመለሱ እንደሚገባ መክረዋል።

“የምዕራብ ትግራይ ችግር ሊፈታ የሚችለው መሬታችን ነው ብለው በኃይል ከያዙት መሬት ሲወጡ ብቻ ነው። የተካሄደው ውጊያ ሰላም የማስከበር ዘመቻ እንጂ የቦታ ማስመለስ አይመስለኝም። ለዚህ ፌደራል መንግሥት አቅጣጫ ሊሰጥበት ይገባል። ሁለተኛው ደግሞ እነዚህ የሰሜን ምዕራብ ተፈናቃዮች ወደኛ እንዲመጡ ያደረጋቸው ሥጋት ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ የገጠር አካባቢዎች 80 ከመቶ የሚሆነው በሻዕቢያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ስለሆነ እነዚህ ሁለት ኃይሎች ወደ ቦታቸው ቢመለሱ ህዝቡ በሰላም ይኖራል የሚል እምነት አለኝ።” ብለዋል።

ሽረ እንዳስላሴ ወደ 150,000 የሚጠጉ የራሷ ነዋሪዎች እንዳላት፣ ዶክተር ቴድሮስ አስታውሰው አስተዳደራቸው ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ያለውን ችግር፣ ከሚመለከታቸው ጋር እየተነጋግሩ ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ይፈፀማሉ ስለተባሉት የግድያ፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት እንዲሁም የማባረር ክሦች፣ የአማራ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህን ለማነጋገር፣ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን፣ የዚህ ዘገባ አዘጋጅ ገብረ ገብረመድህን ጠቁሟል።

ይሁንና ሃላፊው በቅርቡ ስለዚህ ጉዳይ ከቪኦኤ ጋር አድርገውት በነበረ ቃለ ምልልስ፣ “ማፈናቀል የአማራ ባህርይም እሴትም አይደለም፤ አካባቢውም አማራ በስፋት የሚኖርበት ነው” ብለዋል።

“በኃይል ተወስደው ነበር” ሲሉ አቶ ግዛቸው የገለጿቸውን “ወልቃይት ጠገዴና ሌሎችም አካባቢዎችን በምዕራብ ትግራይ ስም መጥራት ትክክል አይደለም” ብለዋል።

ተፈናቀልን ከሚሉና የብልፅግና ፓርቲ ባለሥልጣኖች የሚቀርቡ ጥያቄዎች” አቶ ግዛቸው “ትህነግ” ብለው የጠሩት “ህወሃት ዕድል እንዲያገኝ የሚደረግ የልመና ጥሪ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።

ባለፈው ታህሳስ ከዳንሻ ከተማ 11 የጭነት መኪናዎች ሙሉ እናቶችና ህፃናትን ጭነው ተከዜ ወንዝ ላይ እንደጣሏቸው የዐይን እማኝ ነን ያሉ የዳንሻ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ቪኦኤ የትግርኛ ክፍል ዘግቦ ነበር። የዳንሻ ከተማ ምክትል ከንቲባ “የተባረረ ሰው የለም” ሲሉ በወቅቱ መልስ ሰጥተዋል።

ትግራይ ክልል ውስጥ እየደረሱ ናቸው ስለሚባሉ የማፈናቀል አድራጎቶችም ሆነ ሌሎች የበደልና የጥቃት ክሦች ከፌደራል ሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ሰሞኑን ያደረግናቸው ተከታታይ ጥረቶች ለጊዜው አልተሳኩም።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

የትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮች ሽረ እንዳስላሴ ላይ መፍሰሳቸው ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:13:52 0:00


XS
SM
MD
LG