ለስብሰባው የቀረበው ማብራሪያ “በኢትዮጵያ ሰሜን ክፍል በሚገኘው ትግራይ ክልል ጦርነት እየተካሄደ ነው። ሴቶችና ልጃገረዶች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል። መገናኛ ብዙኃን ባልነበሩበት ሁኔታ ዓለም ምን ያህል የጭካኔ ተግባር እንደሚፈፀም ለመገንዘብ የቻለው ገና አሁን ነው” ይላል።
“በትግራይ ሴቶች ላይ የሚፈፀመው የተቀነባበረ የወሲብ ጥቃት ሆን ተብሎ ለጦርነት መሣሪያነት የሚደረግ ነው” የሚለው ስብሰባው ሲጀመር የቀረበው ማብራሪያ የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑትን ሴቶችና ልጃገረዶች ለማከም የሚችል ሆስፒታል አንድ ብቻ መሆኑን ይጠቁማል።
ትግራይ ውስጥ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ህይወት መጥፋቱን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከየመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ማብራርያው ይናገራል።
ስብሳባው የተጀመረው ከትግራይ በቀረበ የቪድዮ ምስል ሲሆን የወሲብ ጥቃት እንደተፈፀመባት የምትናገር ሴት “ደርሶብኛል” የምትለውን በደል ትገልፃለች። ስሟና ያለችበት ቦታ ለደኅንነቷ ሲባል እንደማይገለፅ ተነግሯል።
“እዚህ የመጣሁት በነበርንበት ቦታ ተኩስ ስለነበር ከተኩሱ ለመሽሽ ነው። አምስት ሆነን ነው ሸሽተን የወጣነው። መንገድ ላይ ትልልቅ ወንዞች ስለነበሩ እዛ ስንደርስ ኑና ውኃ ጠጡ አሉን። አንጠጣም አልናቸው። በሉ ወደዛ እንሂድና ምግብ ብሉ አሉን። እኛ ደግሞ አንበላም አልን። ከዛ ለምን አትበሉም? አትጠጡም? ብለው በዱላ ደበደቡን። እኔን እግሬ ላይ በእሳት አቃጥለው ደፈሩኝ። ከአምስታችን አንዷ ነፍሰ ጡር ነበረች። ሌላዋ ደግሞ የልጅ እናት ናትና እነሱን አልነኳቸውም። እኛን ሁለታችንን ግን ደፈሩን። የያዙንና የደፈሩን የታጠቁ ሰዎች ናቸው።”
አፈርማ ቀለም ያለው የደምብ ልብስ የለበሱ እንደሆኑና አብዛኞቹ አማርኛ እንደሚናገሩ፣ የተወሰኑ ሲቪሎችም እንደነበሩ የተናገረችው የወሲብ ጥቃት ሰለባ የሆነችው ሴት፣ ተመርምራ መፀነሷ እንደተነገራት ገልፃለች።
በግጭት ወቅት የሚፈፀሙ የወሲብ ጥቃቶችን ጉዳይ የሚከታተሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ልዩ ተወካይ ፕራሚላ ፓተን ትግራይ ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት እአአ ካለፈው ህዳር 22 አንስቶ በሴቶች ላይ “ተፈፅሟል” ስላሉት አስከፊ የወሲብ ጥቃት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
“ከግጭት ሁኔታ ጋር የተያያዙ የወሲብ ጥቃቶች ባለፈው የታሪክ ምዕራፍ ተዘግተው መቅረት ያለባቸው ሆኖ ሳለ አለመታደል ሆኖ አንደገና ርዕሰ-ዜናዎች በሆኑበት ወቅት ነው የተገናኘነው። በሰሜኑ ተራራማው ትግራይ ክልል በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ ለማመን የሚያዳግት የጭካኔ ተግባር የታከለበት የወሲብ ጥቃት እየተፈፀመ ነው። በተናጠልና በህብረት እየተፈራረቁ የወሲብ ጥቃት የተፈፀመባቸውን ሴቶች የጤና ሠራተኞች በየዕለቱ እየመዘገቡ ነው። ከተለያዩ ተአማኒ ምንጮች በሚደርሱን ዘገባዎች መሠረት በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ የሚፈፀሙት ጭካኔ የተመላባቸው ዘግናኝ ምስሎች ዓለምን አስደንግጠዋል። አንዳንድ ተጎጂዎች በ21ኛው ምዕት ዓመት በሴቶችና በልጃገረዶች አካላት ላይ የሚፈፀመው ጦርነት ምን ያህል አስከፊና ጭካኔ የተመላበት እንደሆነ አሳይተዋል።”
ፕራሚላ ፓተን አያይዘውም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተጨማሪ የረድዔት ሠራተኞች ሁኔታውን የሚያጠኑ ቡድኖችና ጋዜጠኞች ትግራይ ክልል ውስጥ መግባት በመጀመራቸው ዘግናኝ የወሲብ ጥቃቶች ወሬዎች እየወጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“ወታደሮች ሴቶችንና ልጃገረዶችን ለቀናት ያህል አግተው በተደጋጋሚ እንደሚፈራረቁባቸው፣ እርጉዝ ሴቶችን ሳይቀር እንደሚደፍሩ፣ እናቶቻቸው፣ ልጆቻቸው፤ ሚስቶቻቸውና እህቶቻቸው በአስከፊ ሁኔታ ሲደፈሩ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለከቱ እንደሚያስገድዷቸው የሚገልፁ ዘገባዎች እየወጡ ነው። በርግጥ የግንኙነት መሥመሮች በመዘጋታቸው ለመድረስ አስቸጋሪ በመሆኑና የፀጥታ ስጋትም ስላለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እነዚህን ዘገባዎች በራሱ ለማረጋገጥ አልቻለም። ነገር ግን በኔ እምነት ጭካኔ የተመላባቸው ዘግናኝ የወሲብ ጥቃቶች እንደሚፈፀሙ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰሙ ባሉበት በአሁኑ ወቅት እስከሚረጋገጥ ድረስ ዝም ብለን አናይም። ምናልባትም እነዚህ ጥቃቶች በጣም ጥቂቶቹ ሊሆኑ ይችልሉና።”
“እነዚህ ተጎጂዎች የሚታከሙባቸውና የሚጠለሉባቸው ቦታዎችም ዒላማ እንደሚደረጉ፣ በጤና ሠራተኞችና ስለወሲብ ጥቃቶች በሚዘግቡ ጋዜጠኞች ላይ ዛቻዎች እንደሚደርሱም ተአማኒ ዘገባዎች እየገለፁ ነው” ብለዋል ፓርሚላ ፓተን።
“ትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ግጭት እንዳላበቃ ግልፅ ነው” ብለዋል ፕራሚላ ፓተን። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በህብረት እንዲያካሂዱት የታቀደው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ በፍጥነት እንዲካሄድ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል። የጥምረቱ መርማሪ ቡድን በፍጥነት ወደ ቦታው ተልኮ በመላ የክልሉ ቦታዎች ያለገደብ መድረስ እንዲችል እንዲደረግም ፓተን ጠይቀዋል።
ከግጭት ጋር የተያያዘ የወሲብ ጥቃትን ለመከላከል የተባበረ ጥረት፣ ከመላ የዓለም ማኅብረሰብ ዘላቂ የፖለቲካና የገንዘብ ድጋፍን እንደሚጠይቅ ፓርማላ ፓተን አሳስበዋል።
ፋናየ ሰሎሞን የትግራይ ዳያስፖራ አባል ናቸው። የወሲብ ጥቃት የተፈፀመባቸውን ሴቶች መቐለ ውስጥ በመንከባከብ ላይ ያለውን ማዕከል ለመመሥረት የተደረገውን ጥረት ከሌሎች ጋር ሆነው የመሩ መሆናቸውን በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ ተገልጿል።
ፋናየ ሰለሞን ስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር “ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው። ከቁጥጥር ውጭ የመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለዋል። በሴቶች ላይ “ይፈፀማል” ያሉት በደልንም ዘርዝረዋል።
“የትግራይ ሴቶች በአሁኑ ወቅት የሚያስደነግጥ ዓይነት የወሲብ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ነው። እኔ እንደሚመሰለኝ ይህ የሚደረገው ሆን ተብሎ የትግራይ ሴቶችን ለመጉዳት፣ ክልሉን ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድም ለማናጋት ነው። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ ሴቶችንና ልጃገረዶችን ከገጠሟቸው አበይት ችግሮች አንዱ የሰብአዊ መብት በደል ነው። በአሁኑ ወቅት ሴቶች ከመደፈር ሊያመልጡ የሚችሉበት ቦታ የለም። በቤታቸው፣ በሰፈራቸው፣ በሥራ ቦታቸውና ለገበያ በሚሄዱበት ወቅት የወሲብ ጥቃት ይፈፀምባቸዋል።”
ፋናዬ ሰለሞን የትግራይ ሴቶች ሲደፈሩም፣ በምን መልክ እንደሆነ አብራርተዋል።
“አንዲት ሴት ወታደሮች ለቀናት ያህል እየተፈራረቁ ሲደፍሯት ከቆዩ በኋላ በጋለ ብረት ጉዳት እንዳደረሱባት ገልፃለች። ይህን ሲያደርጉ ደግሞ ለወደፊቱ ልጆች እንዳልትወልጂ ነው ይህን የምናደርገው። ማንኛዋም የትግራይ ሴት አድገው የሚዋጉን ጠላቶችን እንዳትወልድ ለማረጋገጥ ነው እንዳሏት ገልፃለች። ሌሎች ሴቶች ደግሞ የመደፈር ሰቆቃ ከተፈፀመባቸው በኋላ ለቀናት ያህል ህክምና እንዳያገኙ እንደተከለከሉ ተናግረዋል። ዓላማው በኤችአይቪ እንዲያዙ ነው። ወታደሮቹ እነሱን ለመድፈር የተመረጡት ኤድስ ሰላለባቸው እንደሆነ፣ እነሱን አስይዘው ሴቶቹ ደግሞ መላ ማኅበሰሰቡን ኤድስ እንዲያስይዙ ሆን ብለን ነው እንዳሏቸው፣ ዋናው ነገር ግን ጤናማ ልጆች እንዳይወለዱ ለማድረግ መሆኑን እንደነገሯቸው የተደፈሩት ሴቶች ጠቁመዋል።”
ሌሎች የወሲብ ጥቃት ሰለባ የሆኑት ሴቶች ደግሞ የወሲብ ጥቃት በሚፈፅሙባቸው ወቅት “ከትግራይነት ደምሽን ለማፅዳት ነው” እንደሚሏቸው መናገራቸውን ፋናየ ሰለሞን ጠቁመዋል። “በቡድን የፆታ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች በአሁኑ ወቅት ሽባ ሆነው መንቀሳቀስ አይችሉም። የማህፀን መገልበጥ ችግርም ደርሶባቸዋል” ብለዋል ፋናየ ሰለሞን።
ወታደሮቹ ጠልፈው የወሰዷቸውና እዚያው የቀሩ ብዙ ሴቶች እንዳሉ፣ ነገር ግን ማንም እንደማይደርስላቸው ሴቶቹ መናገራቸውን፣ ብዙ የተደፈሩ ነገር ግን፣ በወታደሮቹ “ይደርስብናል” በሚሉት ዛቻ ምክንያት ለመናገር ያልቻሉ ሴቶች መኖራቸውንም ፋናየ ሰለሞን በስብሰባው ላይ ተናግረዋል።
“በአሁኑ ወቅት ትግራይ ክልል ውስጥ ህግና ሥርዓት የለም” የሚሉት ተጎጂዎች ችግራቸውን ሊያመለክቱ የሚችሉበት ክፍል እንደሌለና ህክምና ለማግኘት ሲሄዱ ብቻ እንደሚናገሩ ፋናየ ገልፀዋል። ወታደሮቹ ሴቶቹን ከቤታቸውና ከተለያዩ ቦታዎች እንደሚወስዷቸውና ልጆቻቸው ብቻቸውን ተጥለው እንደሚቀሩም ፋናየ ሰለሞን ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል።
ኬር የሚባለው የረድዔት ድርጅት የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ኤስተር ዋትስ ደግሞ ትግራይ ውስጥ የረድዔት ሥራዎችን ለማከናወን “ይገጥማሉ” ስላሏቸው ችግሮች ተናግረዋል።
“በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ ስንንቀሳቀስ አራት ወይም አምስት አበይት ተግዳሮቶች ይገጥሙናል። አንደኛውና ዋነኛው ተደራሽነት ነው። ተደራሽነት አለን። መሥራት እንችላለን። ሆኖም ትልቅ ተግዳሮት ነው። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ እስከ አምስት የሚደርሱ የተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎች አሉ። ስለሆነም ሁኔታዎች በምትሠራበት አከባቢ ይወሰናሉ። በአንድንድ ቦታዎች ከሁለት ወይም ከሦስት ወታደራዊ አዛዦች ጋር ለመነጋገር ትገደዳለህ። ተደራሽነት ለማግኘት የመደራደሩ ጉዳይ ከወታደራዊ አዛዦቹ ጋር ባለህ ግንኙነት ሊወሰን ይችላል። የስልክ መስመር ስለማይኖር መረጃ የማግኘትና የግንኙነት ችግርም አለ። የየዕለቱ የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ መረጃ ማግኘት ከባድ ነው። ስለሆነም ዋናው ነጥብ የሚሆነው ገደብ አልባ ተደራሽነት ማግኘት ነው።”
ሁለተኛው ደግሞ ትግራይ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ረድዔት የሚያስፈልጋቸው ብዙ መሆናቸውን የጠቆሙት ዋትስ የተገኘው ገንዘብ እጅግ አነስተኛ መሆኑንና የሚፈለገውን ያህል ገንዘብ የማግኘት ችግር መኖሩን ገልፀዋል።
ኤስቴር ዋትስ አያይዘውም የክልሉ የጤና ጥበቃ ሥርዓት አለበት ስላሉት ሁኔታ አብራረተዋል።
“የጤና ጥበቃው ሥርዓት ወድሟል። በተለይም በገጠሮች አከባቢ። 21 ወረዳዎች ውስጥ እየሠራን ነው። ጥናት እያካሄድን ነው። ሴቶችንና ልጃገረዶችን አነጋግረናል። እናም በነዚህ ቦታዎች የነበረው የጤና ሥርዓት አሁን የለም። የጤና ማዕከላት የሉም። መድሀኒት የለም። የጤና ሠራተኞችም የሉም። የግል ደኅንነትን በሚመለከት ከፍተኛ ሥጋት አለ። ስለሆነም የጤናው ሥርዓት በቦታው እንዲመለስ ያስፈስጋል።”
አራተኛው የመሰረታዊ አገልግሎት ጉዳይ ነው ይላሉ ዋትስ።
“አራተኛው የመሠረታዊ አገልግሎቶች መመለስ ጉዳይ ነው። የኤለክትሪክ፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎቶች ችግር መፈታት ይኖርበታል። ትግራይ ውስጥ እንሠራ በነበርበት ወቅት በጣም ሰፊ የሆነ ፕሮግራም ነበረን። የመንደሮች ቁጠባና የብድር ማኅበራት በምንለው መርኃ-ግብር መሠረት ከብዙ ሴቶች ጋር እንሠራ ነበር። አሁን ታዲያ ብዙዎቹ የነበራቸውን ንብረት ሁሉ አጥተዋል። ባንክ የነበራቸውን ገንዘብም ለማውጣት አልቻሉም። ክፍት ባንክ ካለም የኪሎሜትሮች ያህል ርቀት ያለው ሰልፍ ይኖራል። ስለሆነም የመሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ድሮው ይዞታቸው መመለስ ጉዳይ ወሳኝ ነው። የሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ቦታ አለመኖርም ትልቅ ችግር ነው።”
በመጨረሻም በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለማቃለል ተጠያቂነት ወሳኝ መሆኑን፣ ዋትስ አስገንዝበዋል።
“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተባብረው ምርመራ እንዲያካሄዱ መወሰኑ መልካም ነው” ብለው እንደሚስቡ የገለፁት ኤስተር ዋትስ፣ አሁን የሚያስፈገልገው የሀቆቹ መውጣት መሆኑን ተናግረዋል።
ለውጥ የሚፈለግ ከሆነ የሚገኙት ሃቆች በይፋ መገለፅ እንዳለባቸው መክረው የጭካኔ ተግባሮች የፈፀሙ ሁሉ ተጠያቂ መሆንና ፍርድ ፊት መቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛነትን ማየት እንደሚፈልጉም የኬር ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኤስቴር ዋትስ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የወሲብ ጥቃቶችን ባካተቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ “ምርምራ አካሂዳለሁ። ተጠያቂነት እንዲኖርም አደርጋለሁ” ማለቱ የሚታወቅ ነው። ሰብዓዊ ረድዔት እያደረገ መሆኑንም ገልፆ በትግራይና ከዚያም አልፎ የሚያስፈልገውን ረድዔት ለማሟላት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የረድኤት ጥረቱን እንዲያፋጥን ጥሪ አድርጓል።
በዚሁ ቅንብር ላይ ለተነሱት ነጥቦች ከመንግሥት ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።