የዓለም ጤና ድርጅት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ፣ በፌደራሉ መንግሥትና በህወሃት መካከል በተካሄደው ግጭት ሳቢያ የተቋረጠው የጤና አገልግሎት፣ አደገኛ ወደ ሆኑ ተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት ሊያመራ እንደሚችል አስጠንቀቋል፡፡
ግጭቱ በአካባቢው የነበረው የሰብአዊ አገልግሎት መስጫ መስመር፣ እንዲቋረጥ ማድረጉንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚገምተው 4.5 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ እርዳታ የሚፈልግ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከፊሎቹ ህጻናት ናቸው፡፡
አካባቢውን በቅርቡ የጎበኙት የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፣ በርካቶቹ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች የሚሰሩት በከፊል ነው፡፡ የጤና ተቋማት ሠራተኞች በሙሉ ለቀው የሄዱ ሲሆን መሠረታዊ የጤና አገልግሎትም ተቋርጧል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት፣ የአስቸኳይ ጤና ጉዳዮች ኃላፊ፣ ተሬሳ ዘካሪያ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች መቋረጥ በህዝቡ ላይ፣ በተለይም ህጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በመግልጽ እንደሚከተለው አስጠንቅቀዋል፡፡
“እኤአ ካለፈው ዓመት የጥር ወር እስከ ህዳር ወር ባለው ጊዜ፣ ከ400 በላይ ህጻናት ላይ የኩፉኝ በሽታ ተከስቷል፡፡ መደበኛው የክትባት መርሃ ግብር በመቋረጡም ይህ ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል፡፡ የወባ በሽታም እንደዚሁ ከ9ሺ በላይ ህጻናትን ለህመም ዳርጓል። ይህ ከተመጣጠነ የምግብ እጥረት ጋር ሲደመር በህጻናት ላይ የሚደርሰው የወባ በሽታ ሞት እስከ ሶስት እጥፍ ሊያድግ ይችላል፡፡”
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በትግራይ ክልል የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በመላ አገሪቱ ካለው አማካይ ከፍ ያለ ነው፡፡
እስካለፈው ህዳር ድረስ፣ ከ6700 የኮቪድ 19 ተጋላጮች ውስጥ የ47 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቧል፡፡ የኮቪድ 19 የሚሰጠው ምላሽ መጀመሪያውኑ ተዘግቶ ስለነበር እንደገና ለማንቀሳቀስም ሂደቱ አዝጋሚ መሆኑን ዘካሪያ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የተነሳም ከባድ አደጋ የተደቀነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ዘካሪያ የሪፈራል ሆስፒታሎችም በጠና የታተሙ በሽተኞችን መቀበል እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ በአስቸኳይ ሥራ ካልጀመሩ በመከላከል ሊድኑ የሚችሉትም ሆነ ሞትን የሚያስከትሉ የበሽታ ዓይነቶች በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ቀደምሲሉ ከነበሩት አብዛኞቹ የወረረሽኝ ታሪኮች እና ልምድ እንደ ምንገነዘበው፣ አብዛኞቹ የበሽታ መከላከል እንቅስቃሴዎች ሲቋረጡ በከፍተኛ ሁኔታ ሊስፋፉ የሚችሉ በሽታዎች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኮቪድ 19፣ ኮሌራ፣ ወባ፣ ቢጫ ወባ እና እንዲሁም በልማድ የማጅራት ገትር የሚባለው በሽታ ይገኙበታል፡፡ ሌሎች በሽታዎችም ክትትል አይደረግባቸውም፡፡ ይሁን እንጂ የበሽታዎችን አዝማሚያ በትክክል መከታተል በማይቻልበት ሁኔታ የወረርሽኙ መጠን መለካት የምንችልበት መንገድ የለም፡፡ ስለሆነም የእውር ድንበራችንን እየተጓዝን ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት፣ ከሌሎች ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ጋር በመሆን፣ መድሃኒት እና ለጤና ተቋማት የሚሆኑ ተጨማሪ አቅርቦቶችን ወደ ትግራይ ለመላክ መቻሉን ገልጿል፡፡ ይህ በቂ ባለመሆኑም ተጨማሪ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸውም አስታውቋል፡፡
በክልሉ ይበልጥ መንቀሳቀስ የሚቻልበትን መንገድ እና፣ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችም ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታን ጠይቋል፡፡ እስከዛሬ ድረስ፣ በክልሉ የሰብአዊ አገልግሎት ለማዳረስ ከሚያስፈልገው የ9.8 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ያገኘው ከግማሽ ያነሰ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
(በቬኦኤ ዘጋቢ ሊሳ ሽላይን ከጄኔቭ የተላከ ዘገባ ነው)
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡