በትግራይ ክልል፣ በፖለቲካ አመራሮች ዘንድ ይታያል ያለው ክፍፍል እንዳሳሰበው፣ የክልሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት አስታወቀ፡፡
124 ድርጅቶችን በአባልነት ያቀፈው የትግራይ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ባወጣው መግለጫ፣ በክልሉ ከፍተኛ ፖለቲካዊ አመራር መካከል የሚታየው ክፍፍል፣ “የክልሉን ብሎም የሕዝቡን ሰላም ሊያደፈርስ የሚችል በመኾኑ ስጋት ገብቶናል፤” ብሏል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ በርኸ፣ ስለ መግለጫው ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ፣ ፖለቲከኞቹ ልዩነታቸውን በሰላም እንዲፈቱ፤ የፌደራሉ መንግሥትም፣ ከፖለቲከኞቹ አለመግባባት ጋራ ተያይዞ የሚመጣውን ችግር በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያየው ጠይቀዋል፡፡