በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ለገሰች


የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ
የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ቁጥሩ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የጆንሰን ኤንድ ጃንሰን የኮቪድ-19 ክትባት ለገሰች።

ዩናይትድ ስቴትስ በአንዴ የሚሰጥ የሆነው የጃንሰን ኤንድ ጃንሰን 453,600 ክትባት በዛሬው ዕለት የሰጠች ሲሆን ተጨማሪ 504,000 ክትባት ደግሞ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገባ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ክትባቶቹን በዛሬው እለት የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የጤና ማእከል በተከናወነ ስነ ስርዓት ለኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ደኤታ ሰሃሬላ አብዱላሂ አስረክበዋል።

የባይደን ሃሪስ አስተዳደር በዓለም ዙሪያ ኮቪድ-19ኝን ለመዋጋት የሚያደርገው ጥረት አካል የሆነው ይህ የክትባት እርዳታ የገባው ለክትባቱ በፍትሃዊነት መዳረስ በሚሰራው በኮቫክስ አማካይነት መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን የክትባቶቹን ክፍፍል የኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጄንሲ በኃላፊነት እንደሚያስፈጽም መግለጫው አውስቷል።

አምባሳደር ፓሲ ባደረጉት ንግግር ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ህዝብ ጤና እንዲሻሻል ያላት ቁርጠኝነት ያኮራኛል ብለው ዛሬ ከተሰጠው እና በመቀጠልም ከሚገባው የክትባት አቅርቦት ጋር በጠቅላላው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ክትባት መለገሳችን ሀገሬ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያላትን ልዩ ግንኙነት ያሰምርበታል ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጸረ ኮቪድ ምላሽ ለመደገፍ ከ200 ሚሊዮን በላይ አስተዋጽኦ ማድረጓን የኤምባሲው መግለጫ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG