በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጎንደሩ የመንግሥት እና የ“ፋኖ” ውጥረት የሽምግልና ጥረት መጀመሩን ተገለጸ


በጎንደሩ የመንግሥት እና የ“ፋኖ” ውጥረት የሽምግልና ጥረት መጀመሩን ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:08 0:00

· መንግሥት በዘመቻው የሰብአዊ መብቶች መርሖዎችን እንዲጠነቅቅ ኢሰመኮ አሳሰበ

በዐማራ ክልል ጎንደር ከተማ ውስጥ፣ በ“ፋኖ” የዐማራ ታጣቂዎች እና በመንግሥት በኩል ተቀስቅሷል የተባለውን ውጥረት ለማርገብ፣ ሽማግሌዎች ገብተው ውይይት እያደረጉ መኾኑን፣ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አዛውንት ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ገለጹ።

በትላንትናው ዕለት፣ በጎንደር ከተማ በ“ፋኖ” የዐማራ ክልል ታጣቂ ወጣቶች እና በመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል፣ ከፍተኛ ውጥረት እንደነበር የገለጹት እኚኽ አዛውንት፣ ጠዋት ላይ ለተወሰኑ ሰዓታት ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በዐማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እየተካሔደ ነው የተባለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰብአዊ መብቶች ተጽእኖ እንዳያሳድር አሳስቧል።

ትላንት፣ በጎንደር ከተማ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ውጥረት ተከትሎ፣ በአገር ሽማግሌዎች አመቻችነት ዛሬ በተካሔደው ውይይት ላይ ተሳታፊ እንደነበር ጠቅሶ ስሙን እንዳንገልጽ የጠየቀን አንድ ወጣት፣ “የዐማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር” የተባለውን አደረጃጀት ወክሎ በውይይቱ ላይ መገኘቱን ገልጾልናል።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ፣ የማዕከላዊ ጎንደር አስተዳደር ባለሥልጣናት እና ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች በሽምግልና ውይይቱ መሳተፋቸውን፣ ለአሜሪካ ድምፅ የተናገረው ወጣቱ፣ ከተነሡ ሐሳቦች መካከል የተወሰኑትን ዘርዝሯል።

በልዩ ልዩ የዐማራ ክልል ከተሞች ያሉ ታጣቂዎችን፣ ያለአግባብ በመፈረጅ ማሳደድ ተባብሷል፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ ስም ያላቸው ሰዎችን የማፈን እንቅስቃሴም ተደርጓል፤ ሲል ክሥ የሚያቀርበው ወጣቱ፣ ትላንት፣ የጎንደር ከተማንና አካባቢዋን ለውጥረት የዳረገው እንቅስቃሴ መንሥኤም፣ ቅቡልነት የሌላቸው መሰል እንቅስቃሴዎች መኾናቸውን ያስረዳል።

“የዐማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር” የተባለው አደረጃጀት አባል መኾኑን የነገረን ይኸው ወጣት፣ በክልሉ ውስጥ ያለው ውጥረት ረግቦ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ ለዓመታት አከራካሪ የኾኑ ጉዳዮችን ከመፍታት ጀምሮ፣ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ላይ የሚከተላቸው አቅጣጫዎች መስተካከል እንዳለባቸው ይሟገታል።

ወጣቱ በቀጣይ፣ ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋራ ውይይት እንዲደረግ፣ በዕለቱ አቅጣጫ መሰጠቱንም አክሏል።

በዐማራ ክልል የተስተዋለው ግጭት እና ውጥረት የጀመረው፣ ከሚያዝያ ወር መጀመሪያ አንሥቶ ሲኾን፣ ይህም መንግሥት፣ የክልሎች ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ከፌዴራል መከላከያ ኃይል እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋራ እንዲቀላቀሉ መመሪያ ማስተላለፉን ተከትሎ የመጣ ነው።

ይህ ውሳኔ በተላለፈበት የመጀመሪያ ሳምንት ላይ፣ በነዋሪዎች እና በፌዴራል ሠራዊት መካከል ግጭት የተስተዋለ ሲኾን፣ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ከዐማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት እና ከ“ፋኖ” የክልሉ ወጣት ታጣቂዎች ጋራ ግጭት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

በ“ፋኖ” ታጣቂ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል፣ በዐማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ አካባቢ ተቀስቅሶ የነበረው ጸጥታዊ ችግር በእርቅ እንዲፈታ፣ በሃይማኖት አባቶች እና በአገር ሽማግሌዎች በተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት መግባባት ላይ ተደርሶ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን፣ በሚያዝያ ወር አጋማሽ መዘገባችን አይዘነጋም።

የዐማራ ልዩ ኃይል እና የ“ፋኖ” ታጣቂ፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ የነበረ ሲኾን፣ ልዩ ኃይሉ በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወንጀል፣ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ክሥ ይቀርብበታል።

በጎንደር ከተማ ነዋሪ የኾኑና ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን ሌላ አዛውንት፣ ትላንት በከተማው ተፈጥሮ ለነበረው ውጥረት መነሻ ነው ያሉትን ገልጸውልናል።

ከትላንት ጀምሮ፣ በከተማው ውስጥ ተኩስ መሰማቱን፣ መንገዶች እና ሱቆችም ተዘግተው እንደነበር ሌላ አንድ ነዋሪም ነግረውናል።

በውይይቱ እንደተሳተፉ በመረጃው የተጠቀሱትን የመንግሥት ተወካዮች አስተያየት፣ ከዐማራ ክልልም ኾነ ከፌደራል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሓላፊዎች ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

በሌላ በኩል፣ በዐማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እየተካሔደ ነው የተባለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ”፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን ተጽእኖ እና ምልከታ በቅርበት እየተከታተለ መኾኑን፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ትላንት በአወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ያለ መኾኑን፤ በተለይም በሸዋ ሮቢት፣ በአርማኒያ፣ በአንጾኪያ ገምዛ እና በማጀቴ፣ በመከላከያ ሠራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል፣ የተኩስ ልውውጥ እና በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መኖሩን በመግለጫው ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ “በዚኽም ምክንያት፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት የደረሰ መኾኑን፣ እንዲሁም ከደሴ ወደ ዐዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ጊዜያት የተዘጋ መኾኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፤” ብሏል በመግለጫው፡፡ በግጭቱ፣ ሰዎች መሞታቸው ከመጠቀሱ ውጪ፣ በቁጥር ምን ያህል እንደኾኑ አልተገለጸም።

በክልሉ፣ የኮሚሽኑ የክትትል እና ምርመራ ዲሬክተር አቶ ዓለሙ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንግሊዝኛው አገልግሎት በሰጡት ምላሽ፣ በዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ የተኩስ ልውውጦች ሪፖርት እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

“በከባድ መሣሪያዎች ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በዚኽም የተነሣ ሰዎች ሞተዋል፤ የወደሙ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ መረጃ ደርሶናል። መንገድ እየተዘጋ መኾኑንና ውጥረት መኖሩን የሚገልጹ ሪፖርቶች አሉ። እኛም የተሟላ መረጃ እንዳገኘን ሪፖርት እናወጣለን፤” ብለዋል ዲሬክተሩ፡፡

በተጨማሪም፣ በክልሉ ያሉ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን ዳግም የማዋቀር ውሳኔን በመቃወም የተካሔዱ ሰልፎችን መርተዋል፤ አስተባብረዋል የተባሉ የተወሰኑ ወጣቶችንና ከፋኖ ታጣቂ ጋራ ግንኙነት አላቸው በሚል የተጠረጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን፣ ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው ላይ አስፍሯል።

የዐማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ የነበረ ሲኾን፣ ልዩ ኃይሉ፣ በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወንጀል፣ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ክሥ ይቀርብበታል።

ኢሰመኮ በመግለጫው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሔደው ጦርነት፣ በሲቪል ሰዎች ላይ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና ጉዳት ማድረሱን አስታውሶ፤ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ተጨማሪ ግጭቶች፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ አስከፊ ጥሰቶች የሚያስከትሉ መኾኑን በመገንዘብ፣ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች፣ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት እንዲፈቱ፣ ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እና ንግግሮች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

በግጭቱ ስለ ደረሰው ጉዳት ሁሉ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በድጋሚ የጠየቀው ኢሰመኮ፣ በማናቸውም ኹኔታ የሚፈጸሙ እስራቶች፣ ሕግን መሠረት ያደረጉ በተለይም ያላቸውን አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነትና ከመድልዎ ነጻ የመኾን የሰብአዊ መብቶች መርሖዎችን ስለማክበራቸው መንግሥት እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርቧል።

በኢሰመኮ መግለጫ ከፌደራል መንግሥት ኮሙኒኬሽንና ከዐማራ ክልል መንግሥት፣ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

XS
SM
MD
LG