በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታይዋን የዓለም የጤና ድርጅት በሀገሬ ህዝብ የጤና መብቶች ግዴለሽነት አሳይቷል ስትል ወቀሰች


ፎቶ ፋይል፦ ታይዋን

የዓለም የጤና ድርጅት ውሳኔ ሰጪ አካል የሆነው የድርጅቱ ጉባኤ ዛሬ ጂኔቫ ውስጥ ዓመታዊ ስብሰባውን የከፈተ ሲሆን በጉባኤው ላይ እንድትካፈል ያልተጋበዘችው ታይዋን ያልተጠራሁት የድርጅቱ ጉባኤ ቻይና ያደረገችበትን ተጽዕኖ ስለተቀበለ ነው ብላለች።

የታይዋን የወጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ው እና የጤና ሚኒስትሩ ቼን ሲህ ቹንግ ባወጡት መግልጫ የዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት እንደመሆኑ ለሰው ልጆች ሁሉ ጤና እና ደህንነት መጠበቅ መስራት እንጂ ለአንድ አባል ሃገር የፖለቲካ ፍላጎት መበገር የለበትም ብለዋል።

ራስ ገዟን ደሴት ታይዋንን የራሴ ግዛት ነች ብላ የምትከራከረው ቻይና ስለምትቃወም ታይዋን እንደየዓለም የጤና ድርጅት የመሳሰሉ አብዛኞች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል መሆን እልተፈቀደላትም።

በሌላ ዜና ዘ ዎል ስትሪት ጋዜጣ ትናንት ባወጣው ዘገባ የቻይናው ዉሃን የቫይረስ ምርመር ተቋም ባልደረቦች የሆኑ ሦስት ሳይንቲስቶች እአአ በ2019 ህዳር ወር ውስጥ ሆስፒታል ገብተው እንደነበር አመለከተ። ቻይና የመጀመሪያውን በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ ሰው መገኘቱን ይፋ ካደረገችበት ጊዜ በአንድ ወር ቀደም ብሎ ነው። ዘገባው ቫይረሱ የተዛመተው ከተቋሙ ቤተ ሙከራ አምልጦ ነው የሚለውን ጥርጣሬ ሊያቀጣጥለው ይችላል ተብሏል።

ቻይና ቫይረሱ መቀስቀሱን አስቀድማም ሳታውቅ አልቀረችም የሚለው መላምት ሲሰነዘር ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በቀደመው የትረምፕ አስተዳደር መጨረሻ አካባቢ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው የክትትል ሰነድ እንደነበር ይታወሳል። በዚያ ሰነድ ቻይና የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ይፋ ከማድረጉዋ አስቀድሞ በ2019 የክረምት መዳረሳ ወራት ውስጥ በርካታ የተቋሙ ተመራማሪዎች የኮቪድ-19ም የሌሎችም የተለመዱ ከአየር ሁኔታ መለዋወጥ ጋር የሚነሱ በሽታዎች የሚመስል ህመም ታመው እንደነበር የሚያሳምን ምክንያት አግኝተናል ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህንድ ውስጥ ትናንት ብቻ ከአራት ሽህ የሚበልጡ ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት እንደሞቱ የጤና ሚኒስቴሩ አስታወቀ። በዚህም ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከብራዚል ቀጥላ በኮቪድ የተነሳ ከ300,000 በላይ ዜጎቿ ህይወት ያለፈባት ሦስተኛ ሃገር ሆናለች።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮቪድ ምክንያት ማለፋቸው የተመዘገበው ሰዎች ቁጥር ከ590,000 ያለፈ ሲሆን ብራዚል ውስጥ ደግሞ ወደ450 000 እየተቃረበ መሆኑን ከጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርስቲው የኮቪድ-19 መረጃ አጠናቃሪ ማዕከል የተገኘው አሃዝ ያመለክታል።

XS
SM
MD
LG