በርካታ የአውሮፓ አገራት ለፍልስጤም እንደአገር እውቅና መስጠታቸው ለሁለት አገር ምስረታ መፍትሄ አያስገኝም ሲሉ የዋይት ኃውስ ብሔራዊ ደህንነት አማካር ጄክ ሱሊቫን ተናገሩ።
መፍትሄ ለማምጣት "እንዴት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የሚያስረዳ ምክንያት አልሰማሁም" ያሉት ሱሊቫን "ለእስራኤልም ሆነ ለፍልስጤማውያን መፍትሄ የምሆን የሁለት መንግስት ምስረታ ላይ መድረስ የሚቻለው በሁለቱ ወገኖች ቀጥተኛ ድርድር ብቻ ነው" ብለዋል።
ሱሊቫን አክለው አሜሪካም ሆነች በቀጠናው የሚገኙ አረብ መንግስታት ያንን ለማሳካት ሲጥሩ መቆየታቸውን ያብራሩ ሲሆን ከጥቅምት ሰባቱ ጥቃት ጀምሮ ሳይሆን ከዛም በፊት፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትኩረት ያደረጉበት ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሱሊቫን ይህን ያሉት ኖርዋይ፣ አየርላንድ እና ስፔን ለፍልስጤም የአገር እውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ ሲሆን፣ ውሳኔው ለበርካታ አስርት ዓመታት እውቅና ለማግኘት ሲታገሉ የኖሩ ፍልስጤማውያንን አስደስቷል። እስራኤል በበኩሏ በሦስቱ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮቿን ጠርታለች።
በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሁለት መንግስት ምስረታ አስፈላጊ መሆኑን የሚከራከሩ በርካታ የአውሮፓ አገራት፣ ክቅርብ ሳምንታት ወዲህ ለፍልስጤም እውቅና ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።
እስካሁን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት ሁለት ሦስተኛውን የሚይዙ ወደ 140 የሚጠጉ አገራት ለፍልስጤም መንግስት እውቅና የሰጡ ቢሆንም ከምዕራብ ኃያል አገሮች መካከል ግን እስካሁን እውቅና የሰጠ አልነበረም።
የዓለም ከፍተኛ የጦር ወንጀሎች ፍርድቤት ዋና አቃቤ ሕግ በእስራኤል እና በሐማስ መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ መጠየቃቸውን ተከትሎ በእስራኤል እና በዩናይትድስቴትስ መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሷል።
የአረብ አገራት፣ የአውሮፓ አገራት እና ዓለም በጠቅላላ በሁለት መንግስት ምስረታ እንደሚያምን ያብራሩት ሱሊቫን ጉዳዩ በአሜሪካ እና በእስራኤል መካከል ያለ የሁለትዮሽ ጉዳይ አይደለም ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም