የሱዳኑን የእርስ በርስ ጦርነት "በዓለም ከማንኛውም የከፋው ሰብአዊ ቀውስ" ሲሉ የገለጹት የአፍሪካ ህብረት ባለሥልጣናት በዛሬው ዕለት በሰጡት አስተያየት፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየዳረገ መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከሚያዝያ 2023 አንስቶ በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ቁጥራቸው 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ማፈናቀሉን የአፍሪካ ሕብረት እና የአለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ አስታወቋል።
ቀውሱ “የሰብአዊ ረድኤት ተደራሽነትን ከማስተጓጎሉም ባሻገር፣ የምግብ እጥረት እና ረሃብን አስከትሏል” ያሉት ደግሞ በኅብረቱ የሱዳን ጉዳይ ተከታታይ ቡድን ሊቀ መንበር ሞሃመድ ኢብን ቻምባስ ናቸው። ኤክስ በተባለው የማሕበራዊ መገናኛ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ
"ሕፃናት እና ሴቶች ያለማቋረጥ እንግልት ይደርስባቸዋል፤ አረጋውያን እና ታማሚዎች የሕክምና ርዳታ አያገኙም" ሲሉም አክለዋል። “ይህ በዓለም ከሁሉም የከፋው ሰብአዊ ቀውስ ነው” ብለዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የሕጻናት ደኅንነት ተከታታይ ክፍል ከፍተኛ ባለሥልጣን ዊልሰን አልሚየዳ አዳኦ’ም በበኩላቸው፡ ኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ በ2024 ብቻ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ለሕክምና ሆስፒታል የገቡ ሕጻናት ቁጥር ከቀደመው ዓመት በ44 በመቶ መጨመሩን፣ በአጠቃላይም የሕክምና ርዳታ የተደረገላቸው ሕጻናት ከ431 000 በላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እስካሁን መቋጫ ባልተበጀለት በሱዳን ጦርነት፡ ብሔራው ጦር የሃገሪቱን ምስራቃዊ እና ሰሜናዊ ክፍል ሲቆጣጠር፣ ፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ በፊናው፡ በድርቁ ክፉኛ የተጎዳውን አብዛኛውን የዳርፉር ክልል መቆጣጠሩ ይታወቃል። የተባበሩት መንግሥታት በትላንትናው ዕለት ለአካባቢው የሚላከውን ርዳታ በማገድ ቡድኑን ወንጅሏል።
“የሱዳኑ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያበቃ ብቸኛው መፍትሔ በሱዳናውያን መካከል የሚደረግ የፖለቲካ ውይይት እንጂ ወታደራዊ አማራጭ አይደለም” ሲሉ ቻምባስ የኅብረቱን እምነት ገልጸዋል።
መድረክ / ፎረም