በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ሴነተሮች ጉብኘት በሱዳን


ሴንተር ክሪስ ክኩንስ እና ሴንተር ቫን ሆለን ባለፈው ረቡዕ በሱዳን ካርቱም ውስጥ ለጋዜጠኞች ውስጥ መግለጫ ሲሰጡ
ሴንተር ክሪስ ክኩንስ እና ሴንተር ቫን ሆለን ባለፈው ረቡዕ በሱዳን ካርቱም ውስጥ ለጋዜጠኞች ውስጥ መግለጫ ሲሰጡ

በዚህ ሳምንት ሱዳንን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ልዑካን፣ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለሚያደርገው ሽግግርና አገሪቱም ከእዳ ነጻ የምትሆንበትን መንገድ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ሱዳን ከኢትዮጵ ጋራ በድንበርና በአባይ ግድብ ዙሪያ ባላት ውዝግቦችም ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ትናንት ሀሙስ ጧት በተጠ ናቀቀው፣ ያላፉት ሶስት ቀናት፣ የሱዳንን ጉብኝታቸው ሴነተር ክርስቶፈር ኩንስ እና ሴንተር ክሪስ ሆለን፣ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላ ሃምዶክና የሱዳን የሽግግር ልዕልና ምክር ቤት መሪ ጀኔራል አብደል ፈታ ቡርሃንን ጨምሮ፣ ከገንዘብ፣ ከውሃና ከመስኖ ሚኒስትሮች ጋር ተገናኝተዋል፡፡

ውይይቱ ያተኮረው ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ በምታደርገው ሽግግር፣ ስላለባት ውዝፍ እዳ ስረዛ እንዲሁም ከአገሯባቿ ኢትዮጵያ ጋር ባሏት የድንበር እና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ግዙፉ ግድብ ዙሪያ ላይ ነበር፡፡

የአሜሪካ ሴንተሮች ጉብኘት በሱዳን
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:46 0:00

የሱዳን የገንዘብ ሚኒስትር ጅብሪል ኢብራሂም የምክር ቤቱ አባላት ስለተጫወቱት ገንቢ ሚና እንደሚከተለው አመስግነዋል፡፡

"ሁለቱ ሴነተሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ጉብኘቱ የተደረገበት ወቅት እጅግ በጣም ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ለመጨው የፓሪስ ጉባኤም ሆነ ሱዳን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ማዕክል ካለባት የውዝፍ እዳ ነጻ እንድትሆን በማድረግ በኩል ሁለቱ የምክር ቤት አባላት የሚሰጡት ድጋፍ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡"

ሴነተሮቹ በምስራቅ ሱዳን ባሉት የመጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ጎብኘተዋል፡፡

ሴነተር ኩንስ ዩናይትድ ስቴትስ ባላፈው ታህሳስ ወር ሱዳንን ትገኝበት ከነበረው ሽብርተኞችን ከሚረዱ አገሮች ዝርዝር ውስጥ፣ የሰረዘቻት መሆኑን ገልጸው ፣ የተረጋጋችውን ሱዳን ተመልሳ ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ስለጉብኝታቸውም ዓላማ የሚከተለውን ብለዋል፦

"እዚህ ያለነው ካርቱምና ሌሎች አካባቢዎችን በመጎብኘት፣ በሱዳን ላለው መነቃቃትና ሽግግር፣ ያለንን ድጋፍ ለመግለጽ ነው፡፡ አሜሪካ በቅርቡ ለሱዳን ለመስጠት የገባችውን የ700 ሚሊዮን ዶላር የልማትና ድጋፍ እርዳታ ለመከታተልና ለሱዳን ህዝብ ሰላም ደህንነትና ብልጽግ ናን ለማስገኘት ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ለመስማት ነው፡፡"

ሴነተር ኩንስ ሱዳን ለዓመታት ያጣችውን የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ መልሳ ለማግኘት በቅርቡ ያደረገችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀዋል፡፡ ይህንንም ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል

"ሱዳን ወደ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ተመልሳ ለመግባት በምታደርገው ጥረት ለውጥ እያሳየች ነው፡፡ ድሮ የነበሩባት እዳዎች እንዲሰረዙላትና ዓለም አቀፍ ኢንቨርስተሮችን ለመሳብ ለነበሩባት ችግሮች መፍትሄዎች እየተገኙ ነው፡፡ ይህም ስለወደፊቱ ተስፋ ያሳደረብን በመሆኑ ደስተኞች ነን፡፡ ሚኒስትሮቹም የኢኮኖሚ ፖሊስውን አስመልከቶ ጠንካራ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል፡፡"

ኩንስ፣ ሱዳንና ግብጽ ከአባይ የምናገኘው የውሃ ድርሻ ይቀንስብናል በሚል ያላቸውን ስጋት አስመልከቶ ሲናገሩ፣ ሱዳን ግብጽ እና ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለምንም ጥርጥር ግድቡን የመገንባት እና ከግድቡም ውሃ የኤልክትሪክ ኃይል አመንጭታ መጠቀም መብቷ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሱዳንም እንዲሁ የውሃውን ፍሰትም ይሁን ፍሰቱ የሚያስከትለውን የደህንነት ጉዳይ አስመልከቶ ባሉት የቴክኒክ ጉዳዮች የድርሻዋን ተገቢውን መረጃ ማግኘት ይኖርባታል፡፡ ይህንንም አስመልከቶ ግብጽንም ጨምሮ በሶስቱም አገሮች የሚያስማማ የስምምነት ማዕቀፍ መኖር አለበት፡፡

የምክር ቤት አባላቱ ሱዳንን የጎበኙት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አንጋፋው የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልክተኛ ጄፍሪ ፌልትመን ከሚያደርጉት ጉብኘት ቀድመው ነው፡፡

ፌልትመን በአስር ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ሱዳን የተሰደዱበትን፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ጨምሮ ፣ የቀጠናውን ፖለቲካ፣ ደህንነትና ሰአብዊ ጉዳዮች የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ፣ ባላፈው ወር በባይደን አስተዳደር በልዩ ልኡክነት የተሾሙ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ፊልትመን ሱዳን፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራን በመጎብኘት ላይ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን አገራቱን በሚያገናኙ ጉዳዮ ላይ በመነጋገር፣ ቀጠናውን አስመልከቶ ዩናትድ ስቴትስ ያላትን አጠቃላይ ፖሊሲ ያቀናጃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

(በቪኦኤ ዘጋቢ ናባ ሞሃዲን ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የተጠናቀረ ዘገባ)

XS
SM
MD
LG