በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳኖቹ ስብሰባ በኢትዮጵያ


የደቡብ ሱዳንና የሱዳን ተደራዳሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡

በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል በነዳጅ ዘይት ገቢ ክፍፍልና በሌሎችም አጨቃጫቂ ጉዳዮች ላይ የሚካሄዱት ተከታታይ ድርድሮች የአሁኑ ዙር የተጀመረው በከበዱ ቃላት ልውውጥና ከድርድሮቹ ውጤት የመገኘቱ ነገር አጠራጣሪ በሆነ ስሜት መሆኑ ተነገረ፡፡

ሁለቱም ወገኖች ነገር የማክረር ጠባይ እንደሚታይባቸው ፒተር ሃይንላይን ውይይቱ ከሚካሄድባት አዲሳባ ያስተላለፈው ዘገባ ይጠቁማል፡፡

ይህ በአፍሪካ ሕብረት ሽምግልና አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው የአሥር ቀናት ድርድር ዛሬ - ማክሰኞ፣ የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ሲከፈት የደቡብ ሱዳን ዋና ተደራዳሪ ፓጋን አሙም “ኻርቱም አዲስ አበባ ላይ ድርድር ላይ ተቀምጣ እንኳን እየፈፀመችብን ነው” ላሉት የፀብ አድራጎት ክስ አሰምተዋል፡፡

“የሱዳን መንግሥት የጦር ነጋሪት እየመታ በመሆኑ ሥጋት አለን፡፡ ሲሉ እንደምንሰማው በደቡብ ሱዳን ላይ ጦርነት ለመክፈት እየተንቀሣቀሱ ነው፡፡ አሁን እየተነጋገርን ባለንባት ደቂቃ እንኳ የሱዳን መንግሥት እያደረገ ያለው ይህንን ነው” ብለዋል ሚስተር አሙም፡፡

አሙም ይህንን የሚናገሩት በግልፅ ባልተካለለው ዓለምአቀፍ ወሰን አካባቢዎች አዳዲስ ግጭቶች መከሰታቸው እየተሰማ ባለበት ወቅት ነው፡፡ የአየር ድብደባ ሸሽተን መጣን የሚሉና አዲስ ጥቃት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው በርካታ ተፈናቃዮች ደቡብ ሱዳን ውስጥ ወደሚገኙ መጠለያዎች እየገቡ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደት ጉዳዮች ኮሚሽነር አስታውቋል፡፡

የድርድሮቹ የመጀመሪያ ዙር ባለፈው ወር ያለውጤት ከተበተነ ወዲህ አንዳችም አበረታች ለውጥ አለማየታቸውን የደቡቡ ተወካይ አሙም ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

ከደቡብ ሱዳን ለዓለም ገበያ ለሚቀርበው ድፍድፍ ዘይት ወደ ወደብ ማስተላለፊያ ኻርቱም በበርሜል 36 ዶላር [በዛሬ ምንዛሪ ወደ 621 ብር ከ655 ሣንቲም መሆኑ ነው] እንዲከፈላት ስትጠይቅ ደቡብ ሱዳን ግን በበርሜል የምትከፍለው 69 ሣንቲም [ማለትም 11 ብር ከ9151 ሣንቲም] ብቻ መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ጁባ ከዚህ ዋጋዋ ፍንክች እንደማትል ደግሞ አሙም በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡

የድርድሮቹ ዕጣ ፈንታ አጠራጣሪ የሆነበት የአፍሪካ ሕብረት ሁለቱም ወገኖች ከግትር አቋማቸው ይለሣለሱ ዘንድ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግባቸው የሚጠይቅ መግለጫ ትናንት አውጥቷል፡፡

የዘይት ገቢ ክፍፍል፣ የደቡብ ሱዳንን ነፃነት የተከተለው የዜግነትና የወሰን ጉዳዮች እያንዳንዳቸው አጣዳፊ እርምጃ የሚያስፈልጋቸው ነጥቦች መሆናቸውን የአፍሪካ ሕብረቱ መግለጫ አሣስቧል፡፡

XS
SM
MD
LG