የሱዳን ጸጥታ ኃይሎች ትናንት ሰኞ ሰባት ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን የሱዳን ሀኪሞች ማኅበር አስታውቋል፡፡
የሱዳን ደህንነት ሹሙ ለቀውሱ ተጠያቂ የሆኑትን ሰዎች ለፍርድ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡
ትናንት ሰኞ የተገደሉት ሰዎች መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም በተደረጉት ሰልፎች እስካዛሬ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር 71 እንደሚያደርሰው ተነገሯል፡፡
የወታደራዊ መሪ ጀኔራል አልቡርሃን ትናንት ሰኞ ከጸጥታ ኃላፊዎች ጋር አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን ሊመጣ የሚችለውን የሽብርተኝነት አደጋ ለመቋቋም፣ የጸረ ሽብር ኃይል ለማቋቋም ከሥምምነት መደረሱን የሱዳን ልዕልና ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
በመንግሥት የወጣው መግለጫ ሰላማዊውን ተቃውሞ ወደ አመጽ በመቀየር ቀውስ ፈጥረዋል፣ ያላቸውን ወገኖች ተጠያቂ ለማድረግ መታቀዱን አመልክቷል፡፡
ባለሥልጣናቱ በቀውሱ በርካታ የጸጥታ አስከባሪዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሀሙስም አንድ የፖሊስ ጀኔራል ከተቃዋሚዎች በተሰነዘረ ጥቃት በስለት ተወግቶ መገደሉን የሱዳን ባለ ሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
የትናንቱ ጥቃት የተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ዴቪድ ስታተርፊልድ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳታ ዋና ፀኃፊ ሞሊ ፊ ወደዚያው እያመሩ ባሉበት ወቅትና ዋሽንግተን ለወራት የዘለቀው ቀውስ እንዲረገብ ለመሸምገል ጥረት በማድረግ ላይ እያለች መሆኑ ተመልከቷል፡፡