በሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አል በሺር ላይ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመደገፍ አንድ የሃገሪቱ ጋዜጠኞች ቡድን ሥራ ማቆሙን አስታውቋል።
ይህ የሱዳን ጋዜጠኞች መረብ አባላት ዛሬ ከሥራቸው ገበታ ላይ ተነስቶ በመውጣት ያሳዩት ተቃውሞ በምግብና በነዳጅ እጥረት፤ እንዲሁም በዳቦ ዋጋ ድንገት መናር ምክንያት ታኅሣሳ 20 የተቀሰቀሰው እምቢተኛነት አካል ሆኗል።
በሌላ በኩል ግን በሣምንቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኻርቱም ውስጥ የአደባባይ ሰልፍ ሳይታይ ውሏል።
ላአለፉ ቀናት የወጡ ሰልፈኞች ፕሬዚዳንት አል-በሽር እንዲወርዱ ሲጠይቁ ተሰምተዋል። ፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎቹን “ከሃዲዎች” እና “ቅጥረኞች” ሲሉ ቢጠሯቸውም የምጣኔ ኃብት ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ግን ቃል ገብተዋል።
“የሃገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች በሣምንቱ ውስጥ ባልታጠቁ ሰልፈኞች ላይ በሣምንቱ ውስጥ በወሰዷቸው በቀጥተኛ ተኩስ የታጀቡ የኃይል እርምጃዎች 37 ሰዎችን ገድለዋል” ሲል ዓለምአቀፉ የመብቶች ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከትናንት በስተያ፣ ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት “የማምናቸው” ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ አመልክቷል።
ሱዳንን “ጠንካራ” በሚባሉ እጆች ላለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ኦማር አል-ባሺር ምዕራባዊቱ “ዳርፉር ግዛት ውስጥ ከ15 ዓመታት በፊት ተነስቶ የነበረን አመፅ ለማዳፈን በወሰዱት የጭካኔ እርምጃ ‘ፈፅመዋቸዋል’ - በተባሉ - በሰብዕና ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎችና ዘር በለየ ፍጅት” ተከስሰው ሄግ የሚገኘው ዓለምቀፉ የወንጀል ችሎት የእሥር ዋራንት ቆርጦ እያሳደናቸው ይገኛል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ