በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በሱዳኑ ግጭት የጤና ማዕከላት ተዘግተዋል፡ 11 ሚሊዮን ሰዎች የጤና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል” የዓለም ጤና ድርጅት


በሱዳን ሁለት ወራት የዘለቀው ሁከት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ 11 ሚሊዮን ሰዎች ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ፡፡

በሌላም በኩል በሱዳን የ72 ሰዓታት የተኩስ አቁሙ ካበቃ በኋላ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና አካባቢዋ በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ውጊያው ከትናንት ረቡዕ ጧት ጀምሮ ቀጥሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ትናንት ረቡዕ ጀኔቭ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሱዳን ለሁለት ወራት በዘለቀው ግጭት የጤና አገልግሎት ዘርፉ ክፉኛ በመጎዳቱ “11 ሚሊዮን ሰዎች የጤና ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል፡፡

“በግጭቱ በተጎዱ አካባቢ ከሚገኙ የጤና ተቋማት ሁለት ሶስተኛው የሚሆኑት አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው” ያሉት ቴዎድሮስ “በጤና ተቋማት፣ በመድሃኒት መጋዘኖች፣ በአምቡላንሶችና የጤና ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ ህሙማንና የጤና ሠራተኞች ወደ ሆስፒታል እንዳይደርሱ አድርገዋቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“የዓለም ጤና ድርጅት ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጤና ተቋማት ላይ 46 ጥቃቶች መካሄዳቸውን አረጋግጧል” ብለዋል ቴዎድሮስ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣን፣ ባለፈው ሳምንት የዓለም ጤና ድርጅት በሱዳኑ ሁከት ምክንያት እየጨመረ የሚሄደውን የጤና ፍላጎት ለማሟላት 145 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቅ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ጠይቋል፡፡

በሌላም በኩል በሱዳን የ72 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ካበቃ በኋላ፣ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና አካባቢው በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ከትናንት ረቡዕ ጧት ጀምሮ ቀጥሏል::

የሶስት ቀናት የእርቅ ስምምነቱ ትናንት ረቡዕ ጧት እንዳበቃ በካርቱም እና እህት ከተማ በሆነችው ኡምዱርማን የተኩስ ድምጾች ይሰሙ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የውጊያው ማገርሸት በሰላማዊ ነዋሪዎች ዘንድ የነበረውን ፍርሃት በድጋሚ ቀስቅሷል፡፡

የካርቱም ነዋሪ የሆኑት አማር ሃሰን የፈጥኖ ደራሹ ጦር ለበርካታ ጊዜ ሊቆጣጠረው ሞክሮ ባልተሳካላት እና በሱዳን ጦር ቁጥጥር ስር በሚገኘው የወታደራዊ ምህንድስና ክፍል ህንጻ አካባቢ የተኩስ ድምጾችን መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ነዋሪው አክለውም “ረቡዕ ጧት በደቡብ ኦምዱርማን በተለይም በምህንድስናው መምሪያ አካባቢ ከባድ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡

ጥቃቱ ከፈቲሃብ ፣ ከኡም ባዳ ኤል ማንሱራ፣ ከአል ዶሃ፣ አባሳ እና ከሌሎች አካባቢዎች ይሰማ ነበር፡፡” ብለዋል፡፡

ለሶስት ቀናት የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ብዙ ጊዜ የማይገኝ መጠነኛ እፎይታ በማስገኘቱ፣ የካርቱም እና ኦምዱርማን ነዋሪዎች ከቤታቸው በመውጣት ምግብ ለማግኘት ችለው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የደቡብ ኦምዱርማን አጎራባች ሳሌሃ ነዋሪ የሆኑት ማናል ኦስማን ውጊያው ተባብሷል ይላሉ፡፡

አስፈላጊ ሸቀጦች እንደገና በማለቃቸው ቤተሰቦች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት አለመቻላቸውን ኦስማን ገልጸዋል፡፡

ሁኔታውን “አሰቃቂ” ሲሉ የገለጹት ኦስማን ሁሉም ነዋሪዎችን ግን አካባቢውን ለመልቀቅ እየሞከሩ አይደሉም ይላሉ፡፡

“ትልቅ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከተማዋን ውጭ ለቀው መሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ኃላ ቀርተዋል፡፡ ህይወት ለነሱ የተለመደ መስሏል፡፡” ሲሉም ኦስማን የሚታየውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

በደቡባዊ ካርቱም በኦሎምፒክ ስታዲዮም በሠፈሩ የፈጥኖ ደራሽ ወታደሮች ላይ የሱዳን ጦር አየር ኃይል ጥቃቶችን ማድረሱን እማኞች ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ካርቱም አጎራባች ከተማ ማዮ ነዋሪ የሆኑት መሐመድ አብደላ ቢያንስ አንደኛው ቦምብ፣ አል አንዳሉስ አካባቢ የሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት መምታቱን ተናግረዋል፡፡

የካርቱም ነዋሪው ሀሰን ሁለቱ የጦርነቱ ተፋላሚ ወገኖች ውጊያቸውን መቀጠላቸውን ገልጸው ፣ የጤና አገልግሎት ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሀሰን አክለውም “ሰላማዊ ዜጎችና ህሙማን የጤና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡ ይህ አካባቢ ከ60 ከመቶ በላይ የሚሆኑ የህክምና ተቋማት

የሚገኙት ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ሲሆን ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል” ብለዋል፡፡

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ገለጻ እስካሁን በሱዳን ጦርነት ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ተፈናቅለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG