በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ይድረስልን ሲሉ ተማፀኑ


በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ይድረስልን ሲሉ ተማፀኑ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:35 0:00

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከሁለት ዓመት በፊት ሲቀሰቀስ፣ ከትግራይ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን፣ በሱዳን በተፋፋመው ግጭት ምክንያት፣ “ችግር ላይ በመውደቃችን መንግሥት ወደ ሀገራችን ይመልሰን፤” ሲሉ ጠየቁ፡፡

በምሥራቅ ሱዳን፣ ዑምራኩባ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ስደተኞች፣ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ እንደተናገሩት፣ የሱዳን ግጭት ከተጀመረ በኋላ ሁሉም ግልጋሎቶች ተቋርጦባቸዋል፡፡ የስደተኞቹ ማኅበራዊ ጉዳይ አስተባባሪ መምህር አሉላ ወልደ ጅወርጊስ፣ የሱዳኑ ግጭት መጀመሩን ተከትሎ፣ በመጠለያ ጣቢያው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሰብአዊ ድርጅቶች ለቅቀው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚኽ ምክንያት፣ ቀድሞም ችግር የነበረበት የአገልግሎት አቅርቦት በሙሉ መቋረጡንና የጸጥታ ችግሩም በመባባስ ላይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መምህር አሉላን ጨምሮ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ ስደተኞች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡

ወይዘሮ አብርሁ ንጉሠ፣ በምሥራቅ ሱዳን ዑምራኩባ በሚባል የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከሚኖሩት ስደተኞች አንዷ ናቸው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከሁለት ዓመት በፊት ሲጀመር፣ ከሑመራ ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን ይናገራሉ፡፡ መድረሻ በዐጣን ጊዜ፣ መጠጊያችን በኾነችው ሱዳን ውስጥ አሁን ግጭት በመቀስቀሱ፣ ተመልሰን ችግር ላይ ወድቀናል፤ ይላሉ፡፡

በዚኹ የመጠለያ ጣቢያ፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ የኾኑት መምህር አሉላ ወልደ ጅወርጊስ፣ በዑምራኩባ መጠለያ ጣቢያ ከ17 ሺሕ በላይ ስደተኞች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በሱዳን የግጭቱን መቀስቀስ ተከትሎ 15 የርዳታ ድርጅቶች መጠለያ ጣቢያውን ለቅቀው በመውጣታቸው፣ ስደተኞች ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ገብረኣብ ተኸሥተ፣ በመጠለያ ጣቢያው የነበሩት አገልግሎቶች በመቋረጣቸውና የደኅንነት ስጋቱም እያየለ በመምጣቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡

ወይዘሮ አብርሁ ንጉሠም፣ ኹኔታው እየተባባሰ በመምጣቱና የክረምት ወቅትም በመቃረቡ፣ መንግሥት ችግራችንን ተመልክቶ እንዲረዳን ጥሪ እናቀርባለን፣ ብለዋል፡፡

በዚኽ አስቸጋሪ ጊዜ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሊያስበን ይገባል፤ ያሉት ደግሞ መምህር አሉላ ናቸው፡፡

በምሥራቅ ሱዳን ባሉት የቱናይድባህ እና ዑምራኩባ መጠለያ ጣቢያዎች፣ ከትግራይ የተሰደዱ ከ60ሺሕ በላይ ስደተኞች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ ሱዳን፣ እኒኽን ጨምሮ ከ1ነጥብ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እንዳስጠጋች፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር መረጃ ያሳያል፡፡

XS
SM
MD
LG