በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን የትግራይ ስደተኞች የጠፉ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ላይ ናቸው


በሱዳን የትግራይ ስደተኞች የጠፉ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ላይ ናቸው
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:50 0:00

· ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ለማገናኘት እየሠራ ነው

በኢትዮጵያ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እና በትግራይ ላይ የተጣለው እገዳ ፍጻሜ በአገኘበት ወቅት፣ ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩ ቤተሰቦች፣ ከትግራይ ሳይወጡ ከቀሩ ቤተ ሰዎቻቸው ጋራ ለማገናኘት፣ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እየሠራ ነው።

ከኢትዮጵያ ተሰደው ለረጅም ጊዜ በካርቱም የኖሩ የትግራይ ማኅበረሰብ አባላትን፣ ለኹለት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ሸሽተው የወጡ ዐዲስ ስዱዳን(መጻተኞች) እየተቀላቀሏቸው ነው። ጦርነቱ፣ ባለፈው ጥቅምት በተደረሰው የሰላም ስምምነት ቢቋጭም፣ አሁንም ከድንበር አካባቢ ካሉ የስደተኛ መጠለያዎች ወደ ካርቱም የሚመጡ አሉ።

ከእነርሱም አንዱ ጌታቸው ነው። የቪኦኤው ሄንሪ ዊልኪንስ፣ ቤተ ሰዎቹን ፍለጋ ላይ ያለውን ወጣቱን ጌታቸውን አነጋግሯል።

የእርሱንም ኾነ የቤተሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ቪኦኤ እውነተኛ ስሙን አይጠቀምም። በትግራይ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት በቅርቡ በመመለሱ፣ እንደ ጌታቸው ያሉ ስደተኞች፣ በጦርነቱ ወቅት የተለያዩዋቸውን ቤተ ሰዎች በማፈላለግ ላይ ናቸው።

ጌታቸው፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ፣ የትግራይ ኃይል አባል የኾነውን አባቱን አይቶት አያውቅም።

“[አባቴ]በሠራዊት ውስጥ ነበር። ወታደር ነበር። ግን ይኑር ይሙት አናውቅም። መረጃ የለንም። ቤተሰቤም አባቴን ማግኘት አልቻለም። የምጠይቀው ሰው የለም፤” ሲል ጌታቸው ለዊልኪንስ ተናግሯል።

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ባለሞያዎች፣ እንደ ጌታቸው ያሉ ሰዎች ቤተሰባቸውን እንዲያገኙ በመርዳት ላይ ናቸው፡፡ “ቤተሰባቸው ወይም ሌላ የቅርብ ሰው ከጠፋባቸው፣ የሚያገኙበትን አገልግሎት እንሰጣለን። ከውጭ መልእክት እንቀበላለን፤ ከዚኽም እንልካለን፤” ይላሉ በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ባለሞያ የኾኑት አንድሬያስ ሻዲን።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ በትግራይ እንዲንቀሳቀሱ ከተፈቀደላቸው ሰብአዊ ድርጅቶች አንዱ ነው።

በጦርነቱ የተሳተፉ ኹለቱም ወገኞች፣ ሰብአዊ ወንጀል ፈጽመዋል፤ የሚል ክሥ ይቀርብባቸዋል። በትግራይ ተፈጽሟል የተባለው “የዘር ማጽዳት” መጠን ግን እስከ አኹን አይታወቅም። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፥ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብቶች መርማሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ አይፈቅዱም።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የሚፈላለጉ ሰዎችን ለማገናኘት የሚጠቀምበት አገልግሎት፣ በትግራይ የተፈጸመውን ሠቆቃ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ይኖረው እንደሁ ቪኦኤ ጠይቆ ነበር።

“ይህን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ የለኝም። ነገር ግን በሺሕ የሚቆጠሩ፣ በቤተሰብ አባሎቻቸው የሚፈለጉ ሰዎች አሉ። መፍትሔ ያገኘንላቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ጉዳዮች አሉ። በርግጥ፣ መፍትሔ የምንሰጣቸው ጉዳዮች እየጨመሩ ይመጣሉ፤” ብለዋል፣ በሱዳን የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ልኡክ መሪ የኾኑት ፓስካል ኩታት።

ኩታት እንደሚሉት፣ አንድንድ ጉዳዮችን መፍትሔ ለመስጠት፣ ረጅም ጊዜ ይወስዳል። እርሱም መፍትሔ ከተገኘ ነው። ጌታቸው ግን፣ በሻዲን እየተረዳ ፍለጋውን ቀጥሏል። “አያቶቼን ደውዬ፣ አባቴ የት እንዳለ ጠየቅኹ፤ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም።”

“በጦርነቱ ምክንያት ቤተሰቤን ማግኘት አልቻልኹም፤ ካለእነርሱ መኖር ደግሞ አልችልም፤” ይላል ጌታቸው።

ፍለጋው ውጤታማ የመኾን ዕድል የለውም - እርሱ ግን ተስፋ አይቆርጥም።

XS
SM
MD
LG