በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን የጦር ኃይል በካርቱም በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይዞታዎች ላይ ጥቃት አደረሰ


በግጭቱ የቃጠሎ ጭስ ይታያል ካርቱም ሱዳን
በግጭቱ የቃጠሎ ጭስ ይታያል ካርቱም ሱዳን

የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ዛሬ ሐሙስ በአየር እና በመድፍ ጥቃቶች መናወጧን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የአይን አማኞች እና ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ፡፡ የጦር ሠራዊቱ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ይዞታዎችን የደበደበ ሲሆን በርካታ ነዋሪዎች እንደገለጡት ግጭቱ ሌሊት ላይ ነው የጀመረው፡፡ የዛሬው ጥቃት የጦር ኃይሉ በዋና ከተማዋ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር ያሉ ቦታዎችን ለመያዝ ከወራት በኋላ የሰነዘረው ከባድ ጥቃት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

የዛሬው ጥቃት የደረሰው በዚህ ሳምንት በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የሱዳን ጉዳይ ዐቢይ አጀንዳ በሆነበት በአሁኑ ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ትላንት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ከጉባኤው ጎን ለሱዳን የጦር ኅይል አዛዥ ለጄኔራል አብደልፋታህ አል ቡርሃን ግጭቱ እየተባባሰ መሄድ ያሰጋቸው መሆኑን አሳውቀዋቸዋል፡፡

የዛሬውን ውጊያ አስመልክቶ የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ስማቸው ያልተገለጸ ምንጭ እንዳሉት የጦር ሰራዊቱ ካርቱም ውስጥ ካሉ የአማጺው ኃይሎች ጋር ከባድ ውጊያ አካሂዷል፡፡ የጦር ሠራዊቱ ወታደሮች በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተያዙትን የካርቱምን አካባቢዎች በሚለየው ናይል ወንዝ ላይ ያሉ ሦስት ድልድዮችን አቋርጠው ጥቃት ማድረሳቸውን ወታደራዊ የመረጃ ምንጩ አመልክተዋል፡፡

የጦር ሠራዊቱ ባለፈው የካቲት ካደርሰው ከባድ ጥቃት በኋላ ከወንዙ ባሻገር ባለችው ኡምዱርማን አብዛኛውን አካባቢ ተቆጣጥሯል፡፡

በርካታ የኡምዱርማን ነዋሪዎች ከንጋት ጀምሮ ከባድ የመድፍ ተኩስ መኖሩን ጠቅሰው “የመኖሪያ ህንጻዎች ተመትተዋል፡፡ የጦር አውሮፕላኖች ሲበሩም አይተናል” ብለዋል፡፡

ከጄኔራል አል ቡርሃን ጋር የተነጋገሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጉቴሬዝ ጦርነቱ በአካባቢው የመስፋፋት አደጋ መደቀኑን አሳውቀዋቸዋል፡፡ የድርጅቱ ዋናዋ የረድኤት ባለሥልጣን በበኩላቸው “የሱዳን ህዝብ አስራ ሰባት ወራት ሙሉ ስቃዩን ሲያይ ቆይቷል፡፡ አሁንም መከራው አላበቃም“ ብለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG