በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የባህር ውስጥ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠቀም ዓለም አቀፍ ሥምምነት ተፈረመ


የባህር ውስጥ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠቀም ዓለም አቀፍ ሥምምነት ተፈረመ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:28 0:00

ብዙ የተነገረለትና፣ ዘይት ዓሣና ሌሎች የውቅያኖስ ሃብቶችን በዘላቂነት ለመጠቀም ያለመ ዓለም አቀፍ ሥምምነት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲጸድቅ፣ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች እጅግ ተደስተዋል። በድርድሩ የተሳተፉት እንደሚሉት ሥምምነቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉትን በአፍሪካ እና በደቡብ ንፍቀ-ክበብ የሚገኙ ዓሣ አስጋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ቅዳሜ የባህር ውስጥ ኃብቶችን ለመጠበቅና አጠቃቀማቸውም ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ ዓለም አቀፍ ሕግ ሲጸድቅ አንዳንዶች የደስታ እንባ አፍስሰዋል።

አንድ የሳይንስ ባለሙያ ደግሞ “ማንም ሰምቶት የማያውቅ እጅግ አስፈላጊ ዓለም አቀፍ ሥምምነት” ሲሉ ገልጸውታል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በተመድ መድረክ የተፈጸመው ሥምምነት ረጅም ርቀት የሚጓዝ ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ አለው።

በሱዳን ዳርቻ በፖርት ሱዳን ለሚኖረውና እንደ አብደላ ሁሴን ሞሃመድ ያሉ በአፍሪካ ለሚኖሩ ዓሣ አስጋሪዎችም ሥምምነቱ ጠቃሚ ነው።

አብደላ በአካባቢው የሚገኝ የዓሣ ገበያ እንዲካሄድም የሚረዳ ግለሰብ ነው። በማንኛውም ቀን ዓሣ ሲመዝንና አጥንቱን ሲያወጣ ይስተዋላል።

እርሱ እንደሚለው በአፍሪካ የሚገኘው የዓሣ ሃብት በመመናመን ላይ ነው። የአብደላ አስተያየትን የተመድ መረጃዎችም ይደግፋሉ። የእርሱና የማኅበረሰቡ ሕይወት በዓሣ እጥረቱ ችግር ውስጥ ወድቋል።

“ከዚህ በፊት የነበረው የዓሣ ቁጥር ከፍተኛ ነበር። ባህሩ በተለያዩ ዝርያዎች የተሞላ ነበር። ከቅርብ ዓምታት ወዲህ ግን እየቀነሰ መጣ። አሁን ዓሣ ለማግኘት ራቅ ወዳለ ቦታ መጓዝ አለብን” ብሏል አብደላ።

አዲሱ ሥምምነት ጠለቅ እና ራቅ ያሉትን ዓለም አቀፍ የውሃ አካላት የሚመለከት ነው። ከባህር ዳርቻ 200 ማይል ወይም 321 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ያለውን የውቅያኖስ አካል የሚመለከት ነው። ይህ ደግሞ በአፍሪካ ላሉ ዓሣ አስጋሪዎች ርቆ ያለ ቦታ ነው። አዲሱ ሥምምነት ግን፣ ዓሣን ጨምሮ ሌሎችንም በውሃ ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች በዘላቂነት ለመጠቀም ስለሚይሳችል፣ እነ ሞሃመድ ‘ዝርያቸው ጠፍቷል’ የሚሏቸው ዓሣዎችም ወደ ባህር ዳርቻ እንዲመለሱ ያደርጋል።

“የዚህ የባህር ላይ ሃብትን የተመለከተው ሥምምነት አንዱ ጥሩ ጎኑ፣ ህጉ የሚመለከተው ዓለም ዓቀፍ የውሃ አካላን ቢሆንም፣ በባህር ዳርቻ ያሉትንም አገሮች ተጠቃሚ ያደርጋል” ይላሉ ፒው በጎ አድራጊ ድርጅት በተባለውና ሥምምነቱ እንዲደረግ ከፍተኛ አስተዋጾ ባደረገው ድርጅት የሚሰሩት ኒኮላ ክላርክ።

የአፍሪካ ዓሣ አስጋሪዎች በአህጉሪቱ ኢኮኖሚም ሆነ የምግብ ዋስትና ላይ ወሳኝ ሚና አላቸው። የዓለም ባንክ እንደሚለው የዓሣው ዘርፍ ከአፍሪካ ኢኮኖሚ 24 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ ይይዛል።

ማይክል ኢምራን ካኑ በሥምምነቱ ሂደት የአፍሪካውን ተደራዳሪ ቡድንን መርተዋል። ሥምምነቱ የአፍሪካን የዓሣ ምርት ከመጨመሩም በተጨማሪ፣ ለአፍሪካ ሌላ ጠቀሜታ አለው። የስምምነቱ ፈራሚዎች ከውቅያኖሱ የሚገኘውን ሃብት ትርፍ እኩል ይካፈላሉ።

“የአየር ንብረት ለውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያስከትለውን የከፋ ተጽዕኖ በተመለከተ እርምጃ ተወስዷል። ይህም ትርጉም ባለው መንገድ ይፈጸማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሳይንቲስቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማረጋገጥም የአቅም ግንባታ አስፈላጊ ነው” ብለዋል ማይክል ኢምራን ካኑ።

ፒው በጎ አድራጊ ድርጅት እንደሚለው ግን ስምምነቱ የዓሣ ክምችታቸው ቀድሞውንም ከመጠን በላይ እጅግ ለተጎዳው አካባቢዎች ሁሉን አቀፍ መፍትሄ አይሰጥም። “የአዲሱ ሥምምነት አስፈጻሚዎች እነዚህ አካባቢዎች ላይ ካሉ አስጋሪዎች ሥራቸው የዘላቂ ሃብት አጠቃቀም ጥረትን እንዳይጎዳ ቀርበው መነጋገር አለባቸው” ሲሉ የድርጅቱ ኃላፊ የሆኑት ሊዝ ካራን ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የሞሃመድ ማኅበረሰብና እንደነሱ ያሉ ሌሎች አፍሪካውያን፣ ቃል የተገባው የጋራ ተጠቃሚነት በአስቸኳይ እንዲጀመር ይሻሉ።

XS
SM
MD
LG