በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩናይትድ ስቴትስ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ ጉዳት አደረሰ


በሰልማ ከተማ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ የቤት ጣራዎችን ሲነቃቅል፣ የሰዎች ህይወት አጥፍቷል፡፡
በሰልማ ከተማ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ የቤት ጣራዎችን ሲነቃቅል፣ የሰዎች ህይወት አጥፍቷል፡፡

ትናንት ሃሙስ የዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ክፍለ ግዛቶችን የመታው ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ በታሪካዊቱ ሰልማ ከተማ የቤት ጣራዎችን ሲነቃቅል፣ ማዕከላዊ አላባማ ውስጥ ደግሞ ለስድስት ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክኒያት ሆኗል።

የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በመጣል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ባስቀረበት የጆርጂያ ክፍለ ግዛትም ሌላ አንድ ሰው መግደሉ ታውቋል።

ከሴልማ ሰሜን ምስራቅ 66 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው የአላባማዋ አውታጓ ወረዳ ባደረሰው ውድመት ነው 6ቱ ሰዎች መገደላቸው የተረጋገጠው።

ሁለት የገጠር ማሕበረሰቦች መኖሪያዎች የተዘረጉበትን 32 ኪሎ ሜትሮች ቆራርጦ የደረሰው አውሎ ነፋስ ቁጥራቸው አርባ የሚደርስ የመኖሪያ ቤቶችን ማውደሙን የወረዳይቱ የድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ድሬክተር ኧርኒ ባጌት ተናግረዋል።

ባጌት ለአሶሼትድ ፕሬስ ዜና ወኪል እንዳስረዱት በርካታ ተንቀሳቃሽ የመኖሪያ ቤቶች ወደ ሰማይ ያነሳው አውሎ ነፋስ አደጋ ያደረሰባቸው 12 ሰዎች ለድንገተኛ ህክምና ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

የአደጋ ሰራተኞች ትላንት ማምሻው ላይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመፈለግ የወደቁ ዛፎችን ሲቆርጡ ማምሸትታቸውም ተዘግቧል።

"በእርግጥም ከባድ ጉዳት ደርሷል። ይህ በዚህ ወረዳ ውስጥ ካየኋቸው ሁሉ የከፋው ነው” ብለዋል ባጌት።

በጆርጂያዋ ጃክሰንም አንድ ሰው በአውሎ ነፋሱ ወቅት በተሳፈረበት ተሽከርካሪ ላይ ዛፍ ወድቆ ህይወቱ ማለፉን የበትስ ወረዳ ወንጀል መርማሪ ሌሲ ፕሩ ተናግረዋል።

በዚህችው ወረዳ ከአትላንታ ደቡብ ምስራቅ በሚገኝ ሥፍራ አውሎ ነፋሱ አንድ የጭነት ማመላለሻ ባቡር ከሃዲዱ ማሳቱንም ባለስልጣናት ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG