ኢትዮጵያዊው የማራቶን ጀግና የሻምበል አበበ ቢቂላ ፶ኛ ዓመት የሮም ኦሎምፒክ ድል መታሰቢያ በአገር ውስጥና በውጭ ተከብሯል።
በአዲስ አበባ በኢጣልያ የባህል ማዕከል የጀግናውን አበይት ስኬቶች ያመላከቱ በ፻፳ ፎቶግራፎች የተደገፉ መረጃዎች ቀርበዋል። የፎቶ ኤግዚቢሽኑ ለአንድ ወር ያህል ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ከአገር ውጭ ደግሞ፥ አበበ በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ ለአፍሪቃና ለአገሩ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ባገኘበት በኢጣልያ የሮም ከተማ፥ ጳጉሜን ፭ እና መስከረም ፩ ቀን የከተማዋ ከንቲባና ፕሬዘዳንቱ እንዲሁም የሻምበል አበበ ቢቂላ ቤተሰቦችና ታላላቅ እንግዶች በተገኙበት ፶ኛው የድል በዓሉ ተከብሮለታል። በባዶ እግሩ የሮጠበት ጐዳናም በስሙ እንዲጠራ የተሰየመ መሆኑን ከሥፍራው የደረሱ ዘገባዎች አመልክተዋል።
ስለ ማራቶኑ ጀግና የጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔን ትዝታዎች ያካተተውን የስፖርት ፕሮግራም ከዚህ ያድምጡ።