ኤም-ጉሩሽ ተብሎ የተሰየመው ይህ አሠራር ደንበኞች ለሚያገኟቸው አገልግሎቶች ወይም ለሚሸምቷቸው ሸቀጦችና አስቤዛዎች በመላ ሃገሪቱ ክፍያ መፈፀም እንዲችሉ የሚያደርጋቸው ነው።
ባለፈው የአውሮፓ ዓመት የተፈረመው የሰላም ውል አገልግሎቱ በመላ ሃገሪቱ መሰጠት እንዲችል ሁኔታዎችን ያመቻቸ ቢሆንም አሁንም የመሠረተ-ልማት እክሎች ሥጋት እንደደቀኑ መሆናቸው እየተነገረ ነው።
ደቡብ ሱዳን በቴክኖሎጂው ለመራመድ እጅግ ወደ ኋላ መቅረቷ በግልፅ እየታየ ባለበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ አዲስ አሠራር መጀመሩ ብዙዎችን እንዳስፈነደቀ ይነገራል።
በዚያ ላይ አገልግሎቱ የባንክ ሂሣብ መክፈትን ስለማይጠይቅ የበዛውን ደቡብ ሱዳናዊ ሊደርስና ሊያገለግል የሚችል መሆኑም እንደሚያበረታታ የሃገሪቱ የብሄራዊ መገናኛዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ላዶ ዋንዪ ኬኚ ተናግረዋል።
“የሞባይል ገንዘብ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና የገጠሩንም ሕዝብ የሚደርስ በመሆኑ እውነተኛ ስኬት ያደርገዋል። ልንደርሣቸውና በገንዘብ ሥርዓቱ ውስጥም እንዲገቡ የምንፈልጋቸውም እነርሱው ናቸው” ብለዋል ዋንዪ ኬኚ።
ኤም-ጉሩሽ ማለት ኤም-ገንዘብ ማለት ነው። ኤም ከእንግሊዝኛው ሞባይል የመጀመሪያ ሆሄ የተወሰደና ጉሩሽ ደግሞ ከአረብኛው “ገንዘብ” ለማለት።
የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ማይክል ማኩዬይ በእጅ ሥልካቸው ላም ሲገዙ በተግባር አሣይተዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ጥሬ ገንዘብ የማይታይበት ገበያ ይሠራ እንደሆነ ለማሳመን ጊዜ እንደሚወስድ ሲናገሩ “መሠራት ያለበት ትልቅ የቤት ሥራ አለብን። እኔን እራሴን ጨምሮ የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ ማስተማር ያስፈልጋል። ስለኤም-ጉሩሽ ደቡብ ሱዳናዊያንን ማሳወቅ የሚያስፈልገው አሁን ያለው ሁኔታ በቂ ባለመሆኑ ነው” ብለዋል።
ለዓመታት የዘለቀ ጦርነቷ ደቡብ ሱዳንን በእጅጉ አደህይቷታል። በሞባልይ ሥልኮች ሥርጭትም ከሕዝቧ የተሸፈነው 21 ከመቶው ብቻ በመሆኑ በአፍሪካ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሃገር አድርጓታል።
ዛዪን ቴሌኮምዩኒኬሽንስ የሚባለው የኤም-ጉሩሽን አገልግሎት የሚሰጠው ኩባንያ ግን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መጀመር ለደቡብ ሱዳን የአዲስ ዘመን መጀመሪያ እንደሆነ ይናገራል።
ሞባይል ገንዘብ እጅግ ወደኋላ ቀርቶ እየተፍጨረጨረ ላለው የደቡብ ሱዳን ምጣኔኃብት ንግድን በማቀላጠፍ በሺሆች የሚቆጠሩ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
እንዲህ ዓይነቱ ገንዘብ በሞባይል የማስተላለፍ አሠራር ደቡብ ሱዳንን ኬንያን፣ ርዋንዳን፣ ታንዛንያንና ዩጋንዳን ከመሣሰሉ አገልግሎቱን ከጀመሩ የሰነባበቱ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች ጎራ እንደሚቀላቅላት ብዙዎች እምነታቸውን እየገለፁ ናቸው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ